የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በመቀሌ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሣቁሶችን አከፋፈለ

52

መቀሌ ፤ መጋቢት 22/2013 (ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ቅርንጫፉ በኩል በመቀሌ ከተማ ድጋፍ ለሚሹ ከ16 ሺህ በላይ ወገኖች የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሣቁሶች ማከፋፈሉን የቅርንጫፉ ሃላፊ ገለጹ።

ሃላፊው አቶ ብርሃኑ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የተከፋፈሉት ቁሣቁሶች ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ናቸው።

ከተከፋፈሉት ቁሳቁሶች መካከል የዳቦ ዱቄት፣ አልባሳት፣ የፕላስቲክ ድንኳኖችና ምንጣፎች ይገኙበታል።

ድጋፉ የተገኘው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር በመተባበር መሆኑን ሃላፊው ተናግረዋል።

ቅርንጫፉ በተጨማሪ በከተማዋ የንህፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ላለባቸው ቀበሌዎች አስር የውሃ ቦቴ ተሽከርካሪዎችን በመመደብ ከ40 ሚሊዮን በላይ ሊትር ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማቅርቡንም ጠቅሰዋል።

ከ6ሺህ በላይ የተጠፋፉ ወገኖችንም ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ ማድረጉንም አቶ ብርሃኑ  አስታውቀዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል አቶ አብተኪሮስ ኃይሉ በሰጡት አስተያየት፤  የቀይ መስቀል ማህበር የአስቸኳይ የምግብ ድጋፉ አድርሶናል፤ በዚህም ሰብአዊ ተቋም መሆኑን በተግባር አስመስክሯል ብለዋል።

ወይዘሮ ምህረት ኪዳኑ በበኩላቸው ፤ማህበሩ ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው ሌሎችም ተመሣሣይ እገዛ እንዲያድርጉላቸው  መፈለጋቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም