በእግር ኳሱ የመጣው ድል የኢትዮጵያዊያንን አንድነት የሚያጠናክር መሆኑን የተለያዩ አስተያየት ሰጭዎች ተናገሩ

62

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21/2013 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፍ ያስመዘገበችው ድል ኢትዮጵያዊያንን በአንድነት የሚያስተሳስር እና በህብረት የሚያቆም መሆኑን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።


ኢትዮጵያ እአአ በ2021 በካሜሮኑ የአፍሪካ ዋንጫ የውድድር መድረክ ላይ የምትሳተፍበትን ድል አስመዝግባለች።

በድሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ደስታቸውን የገለጹ ሲሆን ከተሰራ የማይመጣ ውጤት የለም ብለዋል በመልእክታቸው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ እንድታልፍ ደማቅ ታሪክ ላስመዘገቡ የብሔራዊ ቡድኑ አመራሮች እና አባላት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተገኘው ውጤትም በርካታ ኢትዮጵያዊያን በጎዳናዎችና አደባባዮች በመውጣት ደስታቸውን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ለኢዜአ ሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች እንዳሉት በኳሱ የተገኘው ድል ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር እና ሁሉም ለአገሩ በጋራ መቆም እንዳለበት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በዚህ ፈታኝ ወቅት ያለ ልዩነት አንድ የሚያደርግ ድል በመገኘቱ ትልቅ ደስታን የሚፈጥር እና የሚያኮራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት በጋራ መቆም ቢቻል ሁሉንም ነገር ማሳካት ይቻላል፤ የአገራችንን መልካም ገፅታ ማሳየት ይቻላል ብለዋል።

በአቢጃን ከኮትዲቯር አቻቸው ጋር ዛሬ የተጫወቱት ዋልያዎቹ 3 ለ1 እየተመሩ በ81ኛው ደቂቃ ጨዋታው ቢቋረጥም፤ በምድባቸው በተመሳሳይ ሰአት በማዳጋስካር ሜዳ የተጫወቱት ኒጀር እና ማዳጋስካር አቻ በመውጣታቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን አረጋግጧል።

በመሆኑም ብሄራዊ ቡድኑ ካሜሩን ላይ ለሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ 11 ማጣሪያን በ9 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም