ሴቶችን በሁሉም መስክ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ አመራሮች ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል

77

ሠመራ፤ መጋቢት 21/2013 (ኢዜአ) ሴቶችን በሁሉም መስክ ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸውን ትርጉም ባለው መልኩ ለማረጋገጥ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ ተናገሩ።

የአለም ሴቶች ቀን በዓል ማጠቃለያ ፕሮግራም ዛሬ በሰመራ ከተማ በተካሄደበት ወቅትሚኒስትር ዴኤታዋ እንደተናገሩት፤ በሀገሪቱ  የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በበተደረገው ጥረት  አበረታች ለውጦች ቢመዘገቡም  የሚፈለገው ውጤት ለማምጣት ብዙ ይቀራል።

ይህ ክፍተት የማህበረሰቡ የአስተሳሰብ ለውጥ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ጉዳይ መሆኑን ገልጸው ለውጥ ለማምጣት በየደረጃው ተከታታይ የህዝብ ንቅናቄ አስተምህሮ ስራዎች ወጥነት ባለው መልኩ ማከናወን ይጠይቃል ብለዋል።

የዘንድሮ የሴቶች ቀን በዓል በሴቶች ውሳኔ ሰጪነት፣ሴቶችና ጎልማሶች ትምህርት፣ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ እንዲሁም የሴቶችና ህጻናት ጥቃት መከላከል ላይ የህዝብ ንቅናቄ ለመፍጠር በሚያግዙ ዝግጅቶች እስከ ቀበሌ ድረስ  መከበሩን ጠቅሰዋል።

በዓሉ ሲከበር ሴቶች ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት መረጋገጥ እንዲሁም ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማስከበር በተከፈሉ መስዋእትነቶችን የተገኙ ስኬቶችን ለማሰብና ቀጣይነት ሊሠሩ በሚገባቸው አጀንዳዎች ዙሪያም መግባባት ላይ ለመድረስም ጭምር እንደሆነ አስረድተዋል።

ከሀገራችን ህዝብ ቁጥር ግማሹን የሚሸፍኑት ሴቶች በታሪክ አውድም ይሁን በየዘርፉ ያሉ ጅምር የልማት እቅዶችን በማሳለጥ እንዲሁም የሀገራቸውን ሁለንተናው ብልጽግና በማረጋገጥ ረገድ ሚናቸው የማይተካ ነው ብለዋል።

ትውልድ ከመቅረጽ አኳያም ሚናቸው የጎላ በመሆኑ ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ኋላቀር አመለካከቶችንና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመዋጋት ለማረም በትኩረት መስራት  እንዳለበት ሚኒስትር ዴኤታዋ አመልክተዋል።

ለዚህም   ከፌደራል እስከ ክልል ብሎም  ቀበሌ ድረስ  የሚገኙ አመራሮች  ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ኤሻ ያሲን በበኩላቸው፤ በክልሉ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ  ልማዳዊ ድርጊቶች በመከላከል ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጅምር ስራዎች እንዳሉ ተናግረዋል።

ሆኖም በተለይም የአርብቶ አደሩ ሴቶች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ተከብሮ ኑሮቸውን  በማሻሻል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ   ዘርፈ- ብዙ ምላሽ የሚያፈልገው ጉዳይ ነው ብለዋል።

ይህም ሆኖ ከተለያዩ  መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በበዓሉ ማጠቃለያ ስነ- ስርዓት  ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡና በራሳቸው ጥረት በማህበር ተደራጅተው የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ የሴቶች ማህበራት ከሚኒስቴሩ የተለያዩ የማበረታቻ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል።

የሴቶች ቀን በዓል ዘንድሮ የተከበረው  በአለም አቀፍ ደረጃ ለ110ኛ ፤በኢትዮጵያ ደግሞ ለ45ኛ ጊዜ መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም