በደሴ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት በይፋ ተጀመረ

98

ደሴ ፤መጋቢት 21/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞንና በደሴ ከተማ አስተዳደር ከ11 ሺህ 900 ለሚበልጡ ዜጎችን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ለማዳረስ ዛሬ በደሴ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በይፋ መስጠት ተጀመረ ።

ክትባቱ ሆስፒታሉ በተጀመረበት ወቅት የዞኑ ጤና መምሪያ  ኃላፊ አቶ አንተነህ ደመላሽ  እንዳሉት ፤ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መጥቷል።

የበሽታው ስርጭት በአሳሳቢ ሁኔታ እየተስፋፋ ቢመጣም ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረገ አለመሆኑ ችግሩን ውስብስብ አድርጎታል ብለዋል።

የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ከዛሬ ጀምሮ በዞኑ ከ8 ሺህ 900 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች  ክትባቱን ለማዳረስ  ወደ ስራ መገባቱን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም በመንግስትና ግል ጤና ተቋም የሚገኙ ጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች፣ ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው፣ ተጋላጭና በእድሜ የገፉ ሰዎች ቅድሚያ ክትባቱ እንደሚሰጥ አስረድተዋል።

በተለይ በጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ቅድሚያ መከተባቸው ያለ ስጋት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለህብረተሰቡ መስጠት እንዲችሉ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡

ክትባቱ ለሁሉም ማድረስ ስለማይችል ህብረተሰቡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በመልበስ፣ ንጽህናን  በመጠቀምና  ርቀቱን በመጠበቅ ከቫይረሱ እራሱን እንዲጠብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን  ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰይፉ ሰይድ በበኩላቸው የበሽታው ስርጭት ሲጨምር የህብረተሰቡ ጥንቃቄ መቀነስ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደረግ በእምነት ተቋሞችና ሰው በሚበዛባቸው አካባቢዎች በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ተሰማርተው ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ላይ መሰማራታቸውን ገልጸዋል፡፡

በመንግስት በኩል የወጣው ህግም ተፈጻሚ እንዲሆን የተቀናጀ ስራ  መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃለፊ አቶ አብዱልሃሚድ ይመር በበኩላቸው፤ በአስተዳደሩ 3 ሺህ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዜጎች ክትባቱን ይወስዳሉ ብለዋል።

ክትባቱን መስጠት የሚችሉ ጤና ባለሙያዎች ስልጠና ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውንም ገልጸዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎች ክትባቱን ቅድሚያ መውሰዳቸው ያለ ስጋት ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ያሉት ደግሞ የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ኃይማኖት አየለ ናቸው፡፡

በሆስፒታሉ 888 ጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ክትባት እንደሚወስዱ ጠቁመዋል።

በሽታው ለመከላከል አሁን ክትባቱን የሚወስዱ ዜጎች በቀጣይም ሁለተኛውን ዙር በወቅቱ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የደቡብ ወሎና ደሴ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም የሆስፒታሉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በተገኘበት ዛሬ  በደሴ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በይፋ የተጀመረው ክትባት በተመሳሳይ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎችና ደሴ ከፍለ ከተሞች ባሉ የመንግስትና ግል ጤና ተቋማት እንደሚቀጥል  ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም