የጅማ ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ ድግሪ ተማሪዎች 20 የንግድ ሼዶችን ገንብተው ለወጣቶች አስረከቡ

102

ጅማ፣መጋቢት21/2013 (ኢዜአ) በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎች በማህበረሰብ አቀፍ ትምህርት 20 የንግድ ሼዶችን ገንብተው በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ለተደራጁ ወጣቶች አስረከቡ።

ተማሪዎቹ የገነቧቸውን ሼዶች በማህበር ለተደራጁ 75 ወጣቶች በድጋፍ አበርክተዋል።

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ጫልቺሳ አመንቴ ለኢዜአ እንደገለጹት ጅማ ዩኒቨርስቲ በማህበረሰብ አቀፍ የትምህርት መርሃ ግብር ልዩ ፍልስፍናው የሚታወቅ ነው፡፡

እንደ ዲኑ  ገለጻ 294 ተማሪዎች በአስር ቡድን በመከፋፈል በሁለት ቀበሌዎች በማህበረሰቡ ውስጥ የስራ አጥነት የሚያስከትለውን የኑሮ ችግር በመረዳት ሼዶቹን ሰርተዋል፡፡

በተማሪዎችና በማህበረሰቡ ተሳትፎ  የተገነቡት 20 የንግድ ሼዶች 900 ሺህ ብር ወጪ የተደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በተማሪዎች የተሰሩት ሼዶች የወጣቶችንና የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ችግር በመፍታት ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የጅማ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ በበኩላቸው የኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመው ትምህርት በክፍል ውስጥ ብቻ ተወስኖ መቅረት እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አክለውም ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹ ችግር ፈቺ ዜጎች እንዲሆኑ ካለው ሚና በላይ የህብረተሰቡን ችግር በመፍታት ውጤት እያስመዘገቡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የሁለተኛ ድግሪ ተማሪ አብዱልከሪም መሀመድ እንዳለው በአካባቢው ያለውን የስራ አጥነት ችግር በመለየት የንግድ ሼዶቹን መገንባታቸውን ገልጻል፡፡

"በከተማው የሚገኙ ባለሀብቶችንና ተቋማትን በማስተባበር ሼዶችን ሰርተን ለስራ አጥ ወጣቶች ማስረከብ ችለናል" ብሏል፡፡

ተማሪ አፈወርቅ ሀጫሉ በበኩሉ "ኩፖኖችን አዘጋጅተን ሽጠናል፤ ህብረተሰቡን አሳትፈናል፣ በዚህም ተሳክቶልን ዛሬ ለማስረከብ ችለናል" ብሏል፡፡

"የስራ አጥነት ችግርን በጥቂቱም ቢሆን ለመቅረፍ የበኩላችንን ሞክረናል" ሲል ተማሪው ገልጻል።፡

በሼዶቹ የርክክብ ሥነ-ስርዓት ላይ የጅማ ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተማሪዎችና የጂማ ከተማ አስተዳደር አካላት ታድመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም