የኢንጂነር ስመኘው ሞት የግድቡን ስራ ከመጨረስ አያግደንም _ አስተያየት ሰጪዎች

53
አዲስ አበባ ሀምሌ 22/2010 የኢንጂነር ስመኘው ሞት ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከግብ ለማድረስ የበለጠ ያተጋናል አሉ ኢዜአ ያነገጋራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ስርዓተ-ቀብር ዛሬ ተፈፅሟል። ከስርዓተ-ቀብሩ በፊት በመስቀል አደባባይ ደማቅ የክብር አሸኛኘት ተደርጓል። በስነ-ስርዓቱ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተገኝተዋል። ኢዜአ ያነጋገራቸው የሽኝቱ ታዳሚዎች በኢንጂነሩ ሞት ልባቸው ቢሰበርም፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ከግብ የማድረስ ከፍተኛ ፍላጎትና መነሳሳት ይታይባቸዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት ኢነጂነሩ ህይወት ያለፈበት መንገድ የህዳሴው ግድብ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ተጨማሪ ትርጉም እንዲኖረው አድርጓል። በእርሳቸው ሞት ሳቢያ በሚፈጠረው ሀዘን የሚሰናከል ነገር እንደማይኖር የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ግንባታውንም በቁጭት ከግብ ለማድረስ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።  በዚህ ረገድ መንግስት ለሚያቀርበው የድጋፍ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነን ብለዋል። የከተማው ነዋሪ የሆኑት አቶ አብረሃም ደረሰ በሰጡት አስተያየት ''እሱ ቢሞትም ስራው ይቀጥላል። እንዳውም በቁጭት የእርሱን ዓላማ ከዳር እናደርሳለን እንደጀመርነው እንጨርሳለን፣  ሀዘናችን ሀዘን ነው ˝ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ እርሳቸውን የሚተኩ ምሁራን እንዳሏት የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች ግድቡ በፍጥነት አልቆ ኢንጂነር ስመኘው በታሪክ እንዲዘከሩ መደረግ አለበት ብለዋል።  ''የፈለገ ነገር ቢሆን እቅዳችንን ታርጌት ሳናደርስ የማንመለስ ነን የኢትዮጵያዊያን፣ አሁንም ቢሆን በማንኛውም ነገር መንግስት በሚጠይቀን በሙሉ ከጎኑ ቆመን ይህን የታሰበውን ነገር ጫፍ ለማድረስ የኢንጅነር ስመኘው  ሃውልቱ በቦታው ቆሞ ታሪክ እንዲዘክራቸው እንፈልጋለን'' ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ገነት አለማየሁ የተባሉ የከተማው ነዋሪ ናቸው፡፡ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ላለፉት ሰባት ዓመታት በሥራ አስኪያጅነት ሲመሩ የነበሩት ኢንጂኒየር ስመኘው በቀለ ባለፈው ሐሙስ መስቀል አደባባይ መኪናቸው ውስጥ ሞተው መገኘታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም