ማህበሩ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ወጣቱ የድርሻውን እንዲወጣ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

54

ባህር ዳር ፤ መጋቢት 20/2013 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄደው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ወጣቱ የድርሻውን እንዲወጣ እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበር ገለጹ።

ማህበሩ  ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ለማስቻል በሚደረገው እንቅስቀሴ ውስጥ የበኩሉን ለመወጣት እንዲያግዘው በደብረ ታቦር ከተማ የምክክር መድረክ  አኳሂዷል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወጣት አባይነህ ጌቱ በመድረኩ እንዳለው፤ ሰላማዊና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ የወጣቱን ህይወት መታደግና ደህንነቱን መጠበቅ ነው።

በዚህም በየደረጃው የሚገኙ ወጣቶች  ምርጫ ለዴሞክራሲ መሰረት በሚጥል መልኩ ለማጠናቀቅ  ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግሯል።

ማህበሩም ወጣቶችን በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና በምርጫ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ፈጠራ በማካሄድ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።

ከማንኛውም ፖለቲካ ወገንተኝነት በጸዳ መልኩ የምርጫውን ሂደት ሰላማዊ ለማድረግ በሚካሄደው እንቅስቃሴ  ማህበሩ የበኩሉን ለመወጣት ተዘጋጅቷል ብላል።

ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን በላይ የማህበሩ አባላትቱንም ፓርቲዎች በሚያቀርቧቸው አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦች በመመስረት የወጣቱን ችግር ሊፈታ የሚችለውን  ለመምረጥ  የማዘጋጀት ስራ  እየተካሄደ መሆኑን ወጣት አባይነህ አስታውቋል።

በተጨማሪም ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ችግር በማውጣት ወደ ተሻለ ደረጃ ያሻግራል የሚለውን ፓርቲ በነጻነት ለመምረጥ የሚያስችለውን ዝግጅት ማድረግ ከሁሉም እንደሚጠበቅም ጠቁማል።

ማህበሩ ከምርጫ ቦርድ ባገኘው ይሁንታ 15ሺህ ወጣቶች ምርጫውን እንዲታዘቡ መመልመላቸውን ጠቁሟል።

"ምርጫ የመንግስት ስልጣን በሃይል የመያዝ ልምድን በማስወገድ በሃሳብ ልእልናና በዴሞክራሲ የሚያምን መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ነው" ያለው ደግሞ የማህበሩ አባል  ወጣት  ነጋ አበባው ነው።

በዚህም እድሜው ለመምረጥ የደረሰና የምርጫ ቦርድ መመሪያን የሚያሟላ ወጣት በሙሉ በምርጫው በመሳተፍ ለዲሞክራሲአዊ ስርዓት ግንባታው የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አመልክቷል።

የክልሉ  ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የወጣቶች ማካተት ንቅናቄና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ አወቀ መንግስቴ እንደገለጹት፤ በዓለም ላይ ጠንካራ ኢኮኖሚ የገነቡ ሀገራት ዴሞክራሲን ያበለጸጉ ናቸው።

ወጣቱም ይህን መሰረታዊ ጉዳይ በመገንዘብ የምርጫውን ተአማኒነት በማረጋገጥ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው የራሱን አሻራ ማሰረፍ አለበት ብለዋል።

መድረኩ በቅድመና ድህረ ምርጫ የሚኖረውን እቅንቅስቃሴ ሰላማዊ በማድረግ ወጣቱ ለራሱ የምትመች ሀገር ለመገንባት ከወዲሁ እንዲዘጋጅ  እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በቀጣይ በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ተመሳሳይ መድረክ በማመቻቸት አባላቱን የማንቃትና በምርጫው ተዋናይ እንዲሆኑ የማያዘጋጅ ስራ እንደሚኖርም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም