በባሌና ጉጂ ዞኖች ለበልግ እርሻ ከ355 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለልማት እየተዘጋጀ ነው

100

ጎባ/ነገሌ፤ መጋቢት 20/2013 ፡- በባሌና ጉጂ ዞኖች በዘንድሮ የበልግ አዝመራ ከ355 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በዋና ዋና ሰብል ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

የባሌ ዞን አርሶ አደሮች የምርት ማሳደጊያ ፣ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በሚፈልጉት ጊዜና መጠን እያቀረበላቸው መሆኑን ሲገልጹ፤ ባለፈው ዓመት በዝናብ እጥረት የቀነሰባቸውን ምርት ለማካካስ በተያዘው የበልግ አዝመራ የተሻለ ለማምረት ማቀዳቸውን የተናገሩት ደግሞ የጉጂ ዞን አርሶ አደሮች ናቸው።

የባሌ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ጽህፈት ቤት   ተወካይ አቶ ፍሰሃ ሽፈራው እንዳሉት፤ በዘንድሮ የበልግ እርሻ ከ206 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ለማልማት ዝግጅት ተጠናቋል።

ምርትን ለማሳደግ የተለያዩ የግብርና አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን እንዲተገብር የተለያዩ የግንዛቤ ስራዎች መከናዋናቸውን ገልጸዋል።


ከአፈር ማዳበሪያ በተጓዳኝ ለበልግ አዝመራው የሚውል 40 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ጠቅሰው፤ የአርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል ብለዋል፡፡

በዞኑ በመደበኛው ከሚካሄደው የእርሻ ስራ በተጓዳኝ ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት በመንግስት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ከ7 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ማልማት መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡ 

በባሌ ዞን በበልጉ ለማልማት ከታቀደው የእርሻ መሬት ከ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተመልክቷል፡፡ 

በዞኑ ሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ሀሰን ሙስጠፋ በሰጡት አስተያየት፤ በዘንድሮ የበልግ እርሻ አስፈላጊውን የማሳ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸው፤ ለዚህም ማዳበሪያና ምርጥ ዘርም በወቅቱ እንደቀረባላቸው ተናግረዋል፡፡


ከዚህ በፊት በማህበራት በኩል የሚቀርብልን ማዳበሪያ ዘግይቶ ስለሚደርሰን ከደላሎች በከፍተኛ ዋጋ ለመግዛት እንገደድ ነበር ሉት ደግሞ ሌላው አርሶ አደር ከተማ አዱኛ ናቸው፡፡


በተመሳሳይ ዜና በጉጂ ዞን 149 ሺህ 834 ሄክታር መሬትን በተለያየ የሰብል ዘር ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡

በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ዘውዴ በቀለ እንዳሉት፤ በዞኑ በየዓመቱ ከመጋቢት 20 እስከ ሚያዝያ 30   የበልግ አዝመራ ወቅት ነው።

በዚህ ወቅት ለማልማት  እየተዘጋጀ ካለው  መሬት  ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡


ለምርት ማሳደጊያም እስካሁን በአርሶ አደሩና በከፊል አርብቶ አደሩ 183 ሺህ 120 ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡

ከተዘጋጀው  43 ሺህ 100 ኩንታል ዘመናዊ ማዳበሪያውስጥም እስካሁን 18 ሺህ 393 ኩንታሉ ለተጠቃሚው መሰራጨቱን አመልክተው፤ በተጨማሪም  1 ሺህ 295 ኩንታል የስንዴ፣ የጤፍና በቆሎ የምርጥ ዘር መከፋፈሉን ገልጸዋል፡፡


በሊበን ወረዳ የጎቢቻ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዲዳ ቦሩ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፈው ክረምት በጥናብ እጥረት በሁለት ሄክታር መሬት ላይ ከዘሩት የስንዴ ሰብል ያገኙት ምርት 12 ኩንታል ብቻ እንደሆነ  አስታውሰዋል፡፡


በተያዘው የበልግ ወቅት ይህንን ለማካካስ ማሳቸውን ደጋግመው በማረስ 3 ኩንታል ማዳበሪያ መግዘታቸውን ተናግረዋል፡፡ 


በዚሁ ወረዳ የሲሚንቆ ቀበሌ ነዋሪ አቶ በዳዳ ገልገሎ ያለፈው ክረምት በዝናብ መዛባት ምክንያት ከጠበቁት 30 ኩንታል የበቆሎ ስንዴና የቦለቄ ምርት ያገኙት ከግማሽ በታች እንደነበር አውስተዋል፡፡

በክረምቱ ያጡትን ምርት ለማካካስ ለበልጉ ሁለት  ሄክታር የማሳ ማዘጋጀታቸውንና  ከዚህም  60 ኩንታል ለማምረት ማቀዳቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም