የምርምር ስራዎች የህብረተሰቡን ችግር እንዲፈቱ በጋራ መስራት ይገባል- ምሁራን

124

ደብረ ማርቆስ፣  መጋቢት 19/2013 (ኢዜአ) ሃብት እና እውቀት ፈሶባቸው በምሁራን የሚሰሩ ጥናትና ምርምሮች የህብረሰቡን ችግር በዘላቂነት እንዲፈቱ በጋራ መስራት ይገባል ሲሉ ምሁራን አስታወቁ።

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ  ሃገር አቀፍ የጤና ምርምር ጉባኤ ከትላንት ጀምሮ እየተካሄደ ነው።

የዩኒቨርስቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አረጉ ይኽይስ እንዳሉት በየዘርፉ የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች ችግር ፈች ቢሆኑም ጥቅም ላይ እየዋሉ አይደለም።

በተለይም በጤናው ዘርፍ በርካታ የማህበረሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ምርምሮች በምሁራን እየተካሄዱ ቢሆንም የሚመለከታቸው አካላት የምርምር ውጤቶቹን ወስደው በመተግበር ረገድ ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ አመልክተዋል።

"በዚህም ከፍተኛ ሃብት፣ ጉልበት፣ እውቀትና ጊዜ የፈሰሰባቸው ጥናትና ምርምሮች መደርደሪያ ላይ ሆነው ያለ አገልግሎት እየቀሩ ነው"  ብለዋል።

በዩኒቨርስቲው የሚካሄዱ ምርምሮች የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው የህዝቡን መሰረታዊ ችግሮች የሚፈቱ ከማድረግ ባለፈ ለተጠቃሚ ደርሰው ለተግባር እንዲበቁ ለማስቻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የምርምር ውጤቶች ተግባራዊ ሆነው የማህበረሰቡን ችግር እንዲፈቱ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንደሚገባቸው  አስገንዝበዋል።

የዩኒቨርስቲው ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ አለም በበኩላቸው ጉባኤው በምሁራን የሚቀርቡ ጥናትና ምርምሮች ወደ ተግባር የሚቀየሩበትን መንገድ ለመቀየስ ዓላማ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በጉባኤው በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተካሄዱ ከ20 በላይ የተመረጡ ጥናቶች ለውይይት መቅረባቸውን ጠቁመው ጥናቶቹ በዋናነት በእናቶችና ህጻናት ጤና አጠባበቅ፣ ጥራቱን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥና የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን አመልከተዋል ።

በተጨማሪም ጉባኤው ጥናቶች እንዴት ወደ ተግባር እንደሚቀየሩ ግንዛቤ የሚያዝበትና አዲስ ተመራማሪዎች ከከፍተኛ ተመራማሪዎች ልምድ የሚካፈሉበት እንደሆነ አስረድተዋል።

"መሰል የጥናትና ምርምር ጉባኤዎች የጤናው ዘርፍ የምርምር ስራዎች እንዲጠናከሩ የጎላ ሚና አላቸው" ያሉት ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርስቲ የፀዳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ መምህር  ብርየ ደሳለኝ ናቸው።

በዘርፉ የሚዘጋጁ ጉባኤዎች በተለይም የምርምር ስራዎች ወደ ተግባር እንዲገቡ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበትና ጀማሪ ተመራማሪዎች እውቀትና ክህሎት እንዲያዳብሩ በማድረግ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ጥናትና ምርምሮች በሚካሄዱበት ወቅት ሀገር በቀል እውቀቶች ላይ ትኩረት በመስጠት ከሳይንስ ጋር አቀናጅቶ ለማህበራዊ ችግር መፍቻ ለመጠቀም በጋራ መምከሩ ወሳኝ እንደሆነ ገልፀዋል።

''ሳይንሳዊ ጥናት ጥራት ላለው የጤና አገልግሎትና ህይወት'' በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ባለው ሀገር አቀፍ ጉባኤ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ ምሁራን እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም