ሁሉን አቀፍ የሴቶችን ተሣትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሴት ምሁራን ሚና ወሳኝ ነው-ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ

191

ድሬዳዋ ፣መጋቢት 19/2013 /ኢዜአ/ ሁሉን አቀፍ የሴቶች ተሣትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሴት ምሁራን ሚና ወሳኝ መሆኑን የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ አስታወቁ።

የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከመላው የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ለተውጣጡ ሴት መምህራንና አመራሮች ያዘጋጀ የውይይት መድረክ በድሬዳዋ ተካሂዷል።

የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ "የሴቶች አመራር ሚናና የኢትዮጵያ ብልጽግና" በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።

ፕሬዚዳንቷ በወቅቱ እንደገለጹት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሴት  ምሁራን  እርስ በእርስ በመደጋገፍና በመረዳዳት ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሣትፎና  ተጠቃሚነት  መረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራትን ለማሳካት የድርሻቸውን ማበርከት ይጠበቅባቸዋል።

በሀገሪቱ ሴቶችን በሁሉም መስክ ለማብቃት የሚደረጉ ጥረቶች ከቤተሰብ መጀመር እንዳለባቸው አመልክተዋል።

"በሀገሪቱ  አሁን ካለው ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳይ አንጻር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚገኙ ተማሪዎች፣ መምህራንና አመራሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት የለውጡን ተግባር ማስፋት ይገባል" ብለዋል፡፡

ሴት መምህራንና አመራሮችን በስፋት ለማፍራትና ለማብቃት፣ ሴት ተማሪዎችን ለመርዳትና ለመደገፍ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው በመተግበር ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በሀገራዊ ለውጡ ሴቶችን በብዛት ወደ አመራርነት የማምጣት የሂደት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"እርስ በእርስ በመደጋገፍና የጋራ የትብብር ማዕቀፍ በመፍጠር እውቀትንና  ልምድን  በመጋራት ወደ ከፍታ ይደረሳል" ብለዋል።

ለተግባራዊነቱ ቅድሚያ በዩኒቨርሲቲዎች ላይ ትኩረት መደረጉን አስታውቀዋል።

የውይይቱ ተሳታዎች በበኩላቸው "በዩኒቨርሲቲዎች የተጀመረው  የስልጠናና ሌሎች  ፕሮጀክቶች  በአመራርነት ላይ የሚገኙ ሴቶችን አቅም ለማሳደግ ያግዛሉ" ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲዎች የጡት ማጥቢያ ማዕከል ችግር መፍታትና ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ህጎች አፈጻጸምን መከታተል እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የኢፌድሪ ሴቶችና ህጻናት ሚኒስትር ወይሮ ፌልሰን አብዱላሂ በ22 ዩኒቨርሲቲዎች እየተካሄደ ያለ ጥናት የሴቶችን ችግር እንደሚፈታ ገልጸዋል።

በየተቋማቱ መገንባት የተጀመረው የጡት ማጥቢያ ማከላት በዩኒቨርሲቲዎችም እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የውይይቱ ዓላማ ሴቶች ራሳቸውን በእውቀት በማብቃትና የእርስ በእርስ  ልምድ  በመለዋወጥ  የተሻለ ለውጥ ለማስመዝገብ የሚችሉባቸውን ጓዳናዎች  መዘርጋት  ማስቻል ነው" ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርት ዶክተር ሐረገወይን ፋንታሁን ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም