በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት ከፍተኛ ሀዘን ተሰምቶናል... የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎችና የሃይማኖት አባቶች

102
ጋምቤላ/ ሀምሌ 22/2010 በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት ከፍተኛ ሀዘን እንደተሰማቸው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎችና የሃይማኖት አባቶች ገለጹ። መንግስት ኢንጅነር ስመኘው በቀለ የሞቱበትን ሁኔታ አጣርቶ ፈጥኖ ለህዝብ ይፋ ሊያደርግ እንደሚገባም ጠይቀዋል ። ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ህልፈተ ህይወት ከፈተኛ ሀዘን ተሰምቷቸዋል። ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ጆብ ፓል በሰጡት አስተያየት የኢንጂነሩን ሞት በመገናኛ ብዙሃን ሲሰሙ ከፈተኛ ድንጋጤና ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው ገልጸዋል። ለኢትየጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ጭምር ኩራት የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራን በግንባር ቀደምነት ሲመሩ የነበሩትን  ኢንጀነር ስመኘው በቀለ እንዲሞቱ ያደረገ አካል ካለ የኢትዮጵያን  እድገት በጽኑ የሚጠላ ነው ብሏል። "ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ለአገር እድገትና ህዝብ መለወጥ እየደከሙ ባሉበት ወቅት ድንገት በመሞታቸው ለኢትዮጵውያን ትልቅ ጸጸትና ሀዘን ነው" ያሉት ደግሞ ሌለው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ንጉሴ ቁርኝት ናችው። የግድቡ ግንባታ በእርሳቸው ሞት ይደናቀፋል ብሎ ያሰበ ካለ ከንቱ ምኞት መሆኑን የገለጹት አቶ ንጉሴ፣ ኢንጂነር ስመኝው ቢያልፉም አገሪቱ ባፈራቻቸው ሌሎች ባለሙያዎች ግድቡ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል። ሌለው የከተማው ነዋሪ አቶ ኡቶው አካይ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት "ኢንጂነር ስመኘው የኢትዮጵያን ህዳሴ ግድብ እውን ለማድረግ ሌት ተቀን እየለፉ ባሉበት ወቅት ህይወታቸው ማለፉ የኢትዮጵያ ህዝብ ቀኝ እጁን እንዳማጣት ይቆጠራል" ብለዋል። በተመሳሳይ በጋምቤላ ከተማ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል። መንግስት የሞታቸውን ምክንያት አጣርቶ ይፋ እስኪያደርግ ድረስ ህብረተሰቡ በትግዕስት ሊጠብቅ እንደሚገባም የሃይማኖት አባቶቹ አሳስበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጋምቤላና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ሊቀ ትጉሃን ቆሞስ አባ ቲቶ አዳነ እንዳሉት ቤተ-ክርስቲያኗ በኢንጅነር ስመኘው ህልፈተ ህይወት ጥልቅ ሀዘን ተሰምቷታል፡፡ "ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሲያከናውኑ የነበሩትን የህዳሴ ግድብ እውን በማድረግ ሁሌም የምናስታውሳቸው ይሆናሉ" አባ ቲቶ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ የተነደፈውን የህዳሴ ግድብ በማከናወን ላይ የነበሩትን የአገር ባለውለታ ድንገት በማጣታቸው ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው የገለጹት ሌላው የሃይማኖት አባት ሼክ ሰይድ አሊ ናቸው። የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ቄስ ኡጁሉ ኡኮክ በበኩላቸው አገሪቱ ወደ ልማትና አንድነት በተመለሰችበት በአሁኑ ወቅት እንዲህ አይነት ድርጊት መፈጸሙ ተገቢ ባለመሆኑ እንደሚያወግዙት ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡም ከመንግስት ጎን በመሆን የተጀመረውን የሰላም፣ የአንድነት፣ የመደመርና የፍቅር ጉዞ ከግብ ለማድረስ የድርሻውን እንዲወጣም ቄስ ኡጁሉ ጠይቀዋል። መንግስት ተደጋገሚ የወንጀል ሙከራዎች እየታዩ እርምጃ በመውሰድ በኩል መዘግየት እየታበት መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣  የኢንጂነር ስመኘውን ሞት ምክንያት አጣርቶ ለህዝብ ይፋ ከማድረግ ባለፈ በተለያዩ አካባቢዎች ወንጀል የሚፈጽሙ አካላትን ተከታትሎ ለፈርድ እንዲያቀርበ ጠይቀዋል
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም