የወይዘሮ አዚዛ አብዲ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

88
አዲስ አበባ ግንቦት 7/2010 የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት/ኦህዴድ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ የወይዘሮ አዚዛ አብዲ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ። በምሥራቅ ሀረርጌ ዞን ጡሎ ወረዳ፣ ሂርና ከተማ የተወለዱት ወይዘሮ አዚዛ ከወጣትነታቸው ጀምሮ ድርጅታቸውንና ህዝባቸውን በተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች ሲያገለገሉ ቆይተዋል:: የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሂርና ተከታትለዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሥነ ሕይወት ሳይንስ ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ፤ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በንግድ አስተዳድር ከግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። በሥራ ዘመናቸውም ከወረዳ ምክትል አስተዳዳሪነት ጀምሮ በተለያዩ የክልል ቢሮ ኃላፊነቶች አገልግለዋል። ከጥቅምት 2009 ዓ.ም ጀምሮ የኦሮሚያ ክልል የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ያገለገሉና የተሰጣቸውን ኃላፊነት በታላቅ የህዝብ አገልጋይነት ስሜት ሲወጡ ቆይተዋል። በኦህዴድ ማዕከላዊና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ፣ በጨፌ ኦሮሚያ ፣ በኢህአዴግ ምክር ቤትም አባል ነበሩ። በወጣትነታቸው ባሳዩት ትጋትና የትግል ተሳትፎ በፍጥነት ያደጉና ወደፊትም ብዙ ይሰራሉ ተብለው የሚጠበቁ አመራር እንደነበሩም ተመልክቷል። ባደረባቸው የልብ ህመም በህንድ አገር ህክምናቸውን ሲከታተሉ የቆዩት ወይዘሮ አዚዛ ከትናንት በስትያ በህክምና ላይ እያሉ ህይወታቸው አልፏል። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመና የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ዛሬ ጥዋት አስከሬናቸውን በክብር የተቀበሉ ሲሆን፤ ስርዓተ ቀብራቸውም ከሰዓት በኋላ በኮልፌ የእስላም መካነ መቃብር ተፈጽሟል። በስርዓተ ቀብራቸው ላይ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ የፓርቲ አባላትና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል። ወይዘሮ አዚዛ አብዲ ባለትዳርና የሶስት ልጆች እናትም ነበሩ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም