ዳመናን የማዝነብ ቴክኖሎጂ በዝናብ ላይ የተመሰረተው የሀገሪቱ ግብርና ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋገር ምሁራን ገለጹ

77

መጋቢት 18/2013( ኢዜአ) ኢትዮጵያ ዳመናን የማዝነብ ቴክኖሎጂ መጠቀም መጀመሯ በዝናብ ላይ የተመሰረተውን ግብርና ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ  ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ሲሰጡ ኢትዮጵያ ደመናን ወደ ዝናብ የመለወጥ ቴክኖሎጂን ገቢራዊ ማድረጓን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ቴክኖሎጂውን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት የሜትሮሎጂና ሃይድሮሎጂ ፋካልቲ ዲን ዶክተር ታደሰ ታጁባ እንዳሉት፤ በአንድ አሜሪካዊ ሳይንቲስት የተገኘውን ደመናን የማዝነብ ቴክኖሎጂን ኢትዮጵያ መጠቀም መጀመሯ ለግብረናው ዘርፍ እድገት የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

በርካታ ያደጉ ሀገራት ከዝናብ፣ ገጸና ከርሰ ምድር ውሀ በተጨማሪ ዳመናን በማዝነብ በግብርናው ዘርፍ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ እንደቻሉ  አስታውሰዋል።

ያደጉ ሀገራት የተጠቀሙበትን ይህን ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ማዋል መቻላችን ለሀገራችን ትልቅ ተስፋ ሰጪና ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች የሚኖረው ፋይዳ ላቅ ያለ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በዝናብ ላይ የተመሠረተ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ታደሰ የቴክኖሎጂው ጥቅም ላይ መዋል ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ፣ ለሃይል አቅርቦትና ለኢንዱስትሪ ልማት መፋጠን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።

ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ግብፅና ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በሚያደርጉት ድርድር ውስጥ አንዱ አከራካሪ ነጥብ ኢትዮጵያ የምትለቀው የውሃ መጠን ጉዳይ በመሆኑ በቴክኖሎጂው በመታገዝ ግብጽን ስጋት እንዳይኖራት እንደሚያስቻልም ጠቁመዋል፡፡

ቻይና፣ አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ህንድና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ሲጠቀሙ የነበሩበት ዳመናን የማዝነብ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ መዋሉ ኢትዮጵያን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኗን የሚያመላክት ነው ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ምሁር ዶክተር ሙሉጌታ ገነኑ ናቸው።

ቴክኖሎጂው ስነ-ምህዳርን በማስተካከል ግድቦችንና ኩሬዎችን በመሙላት በድርቅ ጊዜ በአማራጭነት መጠቀም የሚያስችል እንደሆነም ገልጸዋል።

ሁሉ አቀፍ ዕድገት ሊረጋገጥ የሚችለው በሳይንስና ቴክኖሎጂ ተደግፎ መስራት ሲቻል ነው ያሉት ዶክተር ሙሉጌታ ቴክኖሎጂው ከባቢ አየርን በማስተካከል ለሰውና እንስሳት ምቹ የአየር ሁኔታ የሚፈጥር፣ ለግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በቆላማና በረሃማ አካባቢዎች ድንገት የሚከሰት የሰደድ እሳት አደጋን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያስችላልም ብለዋል።

ቴክኖሎጂው በአቬዬሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ብሩህ ከባቢ ሁኔታን በመፍጠር የበረራ ደህንነትን በማገዙ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል።

"ሲልቨር አዮዳይድ፣ ፖታሽየም አዮዳይድ " እና ጨው ዳመና ላይ በመርጨት ውሃ የመፍጠር ሂደቱ ከመደበኛው የዝናብ መጠን ከ5 እስከ 15 በመቶ ማሳደግ የሚያስችል በመሆኑ ከዘርፉ የተሻለ ጥቅም ለማግኘት ተጨማሪ ጥናትና ምርምር ለማድረግ  በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በሜትሮሎጂና ሃይድሮሎጂ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ቶማስ ቶሬራ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከሌሎች የዓለም ሀገራት አንፃር ሲታይ ተራራማ በመሆንዋ ከፍተኛ የዳመና ክምችት ያላት መሆኑን ተናግረዋል።

የዝናብ እጥረት በሚያጋጥምበት ወቅት ዳመናን በማዝነብ የእንስሳት መኖ ልማትን በማስፋፋት ከዘርፉ  ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

በከርሰና  ገጸ ምድር የውሃ አቅማችን ላይ ደመናን የማዝነብ ቴክኖሎጂ መጠቀም በተለይ በድርቅ ጊዜ ከፍተኛ ጥቅም አለው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ በተጠናና በታቀደ ሁኔታ መጠቀም ከተቻለ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ቆላማና ዝናብ አጠር በሆኑ ሰፊ የሚለማ መሬት ባላቸው አካባቢዎች በዚህ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የምግብ ሰብልም ሆነ ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆኑ ምርቶችን በማልማት ከድህነት ለመላቀቅ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ጨምሮ በሳይንስ ላይ ማተኮሯን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ  ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ላይ ሀገሪቱ  ደመናን ወደ ዝናብ የመለወጥ ቴክኖሎጂን ገቢራዊ ማድረጓ መጥቀሳቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም