የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራትን ማጠናከር ይገባል - ፕሬዚዳቷ

83

ሐረር ፤ መጋቢት 18/ 2013 (ኢዜአ) ፡ -የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራትን በማጠናከር ሀገራዊ ለውጡን ከዳር ለማድረስ መረባረብ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።

ፕሬዚዳንቷ በሐሪሪ ክልል ትናንት ወደ ስፍራው በማቅናት በራሳቸው ተነሳሽነት  የተጸነሰውንና በዩኒቨርሲቲ የሚማሩ ሴቶችን ለማብቃት የሚያግዘውን" ፕሬዝዳንሺያል ሜንተርሺፕ" ፕሮጀክትን በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስጀምረዋል፤ በሐረር ለሴቶች የሚደረጉ ድጋፎችንም ተመልክተዋል።

ፕሮጀክቱ  በሐረማያ  ጨምሮ በ11 ዩኒቨርሲቲዎች   የሚማሩ ሴት ተማሪዎችንና  መምህራንን አቅም በማሳደግ ብቁ እና ተወዳዳሪ እንደሆኑ የሚጠቅም መሆኑን ፕሬዚዳንቷ  በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ ለሴቶች ልዩ ድጋፍና ክትትል በማድረግ በትምህርታቸውና በአመራር መስክ ለማብቃት ይሰራል፤ ተማሪዎች መሰናከል ሳይገጥማቸው ትምህርታቸውን  አጠናቀው እንዲወጡ ያግዛቸዋል።

ለሁለት ዓመታት የሚተገበረው ፕሮጀክቱ 2000 ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግና አንድ ሶስተኛው ወንዶች እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።:

የሚንተርሺፕ ፕሮጀክት ወደፊት የተጓዙ የኋላዎቹን ወደ ፊት እንዲመጡ በመደገፍና በስራ አለም ያሉትን ወደ አመራርነት በማብቃት ሴቶች በሁሉም መስክ ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

ሴችን ማስተማር ሀገርን መገባትና መለወጥ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ ሴቶችን በሁሉም መስክ መደገፍ ሀገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ጎዳና የሰመረ ለማድረግ  የጎላ አስትዋጽኦ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

ለሴቶች የተከፈተው የለውጥ ጎዳና በእለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች በማስፋት ዳር በማድረስ ተግባር ላይ ለማዋል ርብርቡ ሊጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።

በፕሮጀክቱ አካሄድ ዙሪያ ፕሬዚዳንቷ  ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ  ሴት ተማሪዎችና  መምህራን  ጋር  ተወያይተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተመቻቸው ፕሮጀክት ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሐረር ከተማ ሴቶችን ለማብቃትና  የተቸገሩትን ለመደገፍ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ተግባራትን ተመልክተዋል።

በተለይ በምስራቅ ኢትዮዽያ ክፍል ለሚገኙ ሴቶች ህክምና እየተሰጠ የሚገኘውን የፌስቱላ ሆስፒታልን እንቅስቅሴ አበረታትተዋል።

ጥቃት ለሚደርስባቸው ሴቶችና ህጻናት ማገገሚያ ማዕከል እንዲሁም የ"ሸሪፍ" የግል ሙዚየምና የ"ኢናይ አበዳ " የባህላዊ እደ ጥበብ ማሰልጠኛ ኮሌጅ በፕሬዚደንቷ ተጎብኝቷል።

በሥነ-ሥርዓቱ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ ጨምሮ የተለያዩ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም