የበጋ የስንዴ መስኖ ስራ በታቀደው መሰረት ውጤታማ እየሆነ ነው…አቶ ሽመልስ አብዲሳ

82

ጅማ መጋቢት 17/2013  (ኢዜአ) አርሶ አደሮች በበጋ መስኖ ውጤታማ ስራ ማከናወን እየቻሉ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ሺመልስ አብዲሳ ገለጹ።

ፕሬዝዳንቱ ዛሬ ከሰአት ጂማ ዞን ሰቃ ወረዳ በመገኘት የአርሶ አደሮችን የምርት ሒደት ጎብኝተዋል።

አቶ ሽመልስ በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለጹት የመስኖ ስንዴ ፕሮጀክት ዋነኛ አላማው እያንዳንዱን ሰው በምግብ እህል እራሱን ማስቻል ነው።

“ሀገራችን በምግብ እህል እራሷን እንድትችል ማድረግ ከተቻለ ሌላው ልማት የቀለለ ይሆናል” ብለዋል፡፡

በመጀመሪያው ዙር 160ሺ ሄክታር መሬት ለምርት መብቃቱን ገልጸው “በሁለተኛው ዙር ደግሞ 220ሺ ሄክታር መሬት ለምርት ይበቃል” ብለዋል፡፡

ከስንዴ ምርታማነት አንጻር የበጋው የስንዴ ምርት በአስገራሚ ሁኔታ ምርታማ እንደሆነ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ በሄክታር ዝቅተኛው 48 ኩንታል ሲሆን ከፍኛው 92 ኩንታል ድረስ መመረት መቻሉን እንደተመለከቱም ተናግረዋል።

ከውጭ ይገባ የነበረውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው ክልሉ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ሶስት ሚሊዮን ስንዴ አምርቶ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ሀላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በበኩላቸው “አርሶ አደሩ ለስንዴ ምርታማነት ላደረገው አስተዋጽኦ እውቅናና ምስጋናም ይገባዋል” ብለዋል።

አርሶ አደሩን የገበያ ችግር እንዳይገጥመውና ተጠቃሚነቱን ይበልጥ ለማሳደግም ከፌዴራል መንግስት ጋር እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም