ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሎሳንጀለስ አምርተዋል

187
አዲስ አበባ ሀምሌ 22/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የዋሸንግተን ዲሲ ቆይታቸውን አጠናቀው ወደ ሎሳንጀለስ አምርተዋል። ዶክተር አብይ በሎሳንጀለስ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ መጪ እድል እና የዜጎች ተሳትፎ ላይ እንደሚነጋገሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በዋሽንግተን ዲሲ ያካሄዱት ተከታታይ ውይይት በስኬት መጠናቀቁ ተገልጿል። በዋሽንግተን ዲሲ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች የተሳተፉባቸው 13 መድረኮች በስኬት እንደተከናወኑም በመግለጫው ተጠቅሷል። እነዚህ መድረኮች በኢትዮጵያውያን እና በመንግስት መካከል የነበረው ግንብ ፈርሶ የአንድነት እና የፍቅር ድልድይ የተገነባባቸው እንደሆኑም ተመልክቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሎስአንጀለስ የውይይት መድረክ በተጨማሪ በሚኒሶታ ቆይታ እንደሚኖራቸውም ተጠቅሷል። በዋሽንግተን በተካሄደ የማጠናቀቂያ ስነ-ስርዓት ላይ መድረኮች እንዲሳኩ ድጋፍ ላደረጉ ለአሜሪካ መንግስት የተለያዩ ተቋማት፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሚኒስቴሩ ምስጋናውን አቅርቧል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ “የጥላቻና የልዩነት ግንብን አፍርሰን የፍቅርና የአንድነት ድልድይ እንገነባለን” በሚል መሪ ሀሳብ በዋልተር ኢ ዋሽንግተን የስብስባ ማዕከል ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር መወያየታቸው የሚታወስ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ በሚኖራቸው ቆይታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው እየተካሄደ ላለው ሁለንተናዊ ለውጥ አካል ሆነው ለአገሪቱ ልማትና እድገት አስተዋጽኦ በሚያደርጉበት ሁኔታ እየተወያዩ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም