ባህር ዳርን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ ይገባል- ኢንጂነር አይሻ መሃመድ

96

ባህርዳር መጋቢት 17/2013 ( ኢዜአ) -የባህር ዳር ከተማን ጽዳቷን በመጠበቅና በማስዋብ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ ይገባል ሲሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር  አይሻ መሃመድ አስታወቁ።

የአማራ ወጣቶች አረንጓዴ ፎረም አባላት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ የጽዳት ዘመቻ አካሂደዋል።

ሚኒስትሯ ኢንጂነር  አይሻ መሃመድ በወቅቱ እንደገለጹት ባህር ዳር የአባይ ወንዝና የጣና  ሃይቅ መገኛ ከተማ መሆኗ ለቱሪስት መስህብነት የታደለችና ተመራጭ ያደርጋታል።

ከተማዋን ውብ፣ ለነዋሪዎቿና ለጎብኝዎች ምቹ ለማድረግ የደረቅና የፍሳሽ ቆሻሻን  የማስወገድ ተግባሩን ማዘመን እንደሚገባ አመላክተዋል።

"ይህ ካልሆነ  የከተማዋ ሳቢነትና ውበት ከመቀነስ ባሻገር ለነዋሪዎቿ የጤና ጠንቅ መሆኗ የማይቀር ነው" ያሉት ሚኒስተሯ  ከተማዋ ያለችበትን ሁኔታ ተገንዝቦ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል ።

አሁን ባለው የዓለም ስልጣኔ ደረጃ ቆሻሻን ወደ ሃብትነት በመቀየር ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለገቢ ማስገኛና ለቴክኖከሎጂ ሽግግር በማዋል ከተሞችን ጽዱና አረንጓዴ ማድረግ  እየተለመደ መሆኑን ጠቁመዋል ።

የከተማዋን ጽዳትና ውበት በመጠበቅ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የባህር ዳር ከተማ መስተዳደር፣  ነዋሪዎችና ወጣቱ ከተማዋ ተፈጥሮ ያደላትን ጸጋ በመጠቀም  የበለጠ ውብና ማራኪ ለማድረግ ጽዳትን የዘወትር ተግባር አድርገው መስራት እንደሚኖርባቸው ሚኒስትሯ አሳስበዋል።

"የአማራ ወጣቶች አረንጓዴ ፎረም ህዝቡን በማሳተፍ ከተማዋን ጽዱ ለማድረግ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚመሰገንና አርያ ሊሆን የሚገባው  ነው" ብለዋል ሚኒስተሯ።

"የከተማ ነዋሪ ከመነዋሪያው በ20 ሜትርና የንግድ ተቋማት ደግሞ በ40 ሜትር ክልል የሚገኝ ቦታ እንዲያጸዱ ለማድረግ ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው" ያሉት ደግሞ የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሣህሉ ናቸው።

ከዚህ ቀደም ከተማዋን የበለጠ ለማስዋብና አረንጓዴ ለማድረግ  በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን  ገልጸው  "የዛሬው የጽዳት ዘመቻ የበለጠ ትኩረት ለመስጠትና ንቅናቄ ለመፍጠር ያለመ ነው" ብለዋል።

የአማራ ወጣቶች አረንጓዴ ፎረም  ከተሞችን ከማጽዳትና ከማስዋብ ባለፈ  ጠንካራ ሀገራዊ ትስስር እንዲኖር በማሰብ እየሰራ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የፎረሙ ፕሬዝዳንት ወጣት በለጠ ወዳጀነህ ነው።

ፎረሙ በቀጣይ ከአማራ ክልል በተጨማሪ አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ክልሎች ላይ መሰል የከተሞች ጽዳት ለማካሄድ እየሰራ መሆኑን  አመላክቷል።

"ፎረሙን ሀገራዊ ለማድረግ እየሰራን ነው" ያለው ወጣት በለጠ ፎረሙ ከተሞችን ከማስዋብ ባለፈ ጥሩ አስተሳሰብና ጠንካራ ሀገራዊ ትስስር እንዲኖር ለማስቻል ዓላማ ይድርጎ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

በጽዳት ዘመቻው ላይ ሚኒስትሯን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ የስራ ሃላፊዎች፣ የከተማዋ ነዋሪዎችና  የአማራ ወጣቶች አረንጓዴ ፎረም አመራሮችና አባላት መሳተፋቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም