የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ዜጎች የትምህርት ተደራሽነት ማረጋገጥ ይገባል

93

መጋቢት 17 ቀን 2013 (ኢዜአ) የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች የትምህርት ተደራሽነት እንዲረጋገጥላቸው ፍቅር የኢትዮጵያ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ብሔራዊ ማኅበር ጠየቀ።

ማኅበሩ መጋቢት 21 ቀን የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የአዕምሮ ውስንነት ቀን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

ፅንስ ከመፈጠሩ በፊት ከወላጆች የሚተላለፈው ዘረመል በእጥፍ ሲጨምር በሚወለደው ህጻን ላይ የአዕምሮ እድገት ውስንነት የሚከሰትበት ዕድል የሰፋ መሆኑን የሕክምና ጥናቶች ያሳያሉ።

በተጨማሪም ነፍሰ ጡር እናት በእርግዝና ጊዜዋ መውሰድ የሌለባትን መድሃኒቶች ከወሰደች፣ ለአዕምሮ ጭንቀት የሚዳርጉ ሁኔታዎች ውስጥ ከሆነችና በተዛማጅ ችግሮች ሳቢያ ሊከሰት እንደሚችልም እንዲሁ።

የማኅበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ምህረት ንጉሴ እንደገለጹት የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ህጻናት እነሱን በሚመጥን መልኩ እንክብካቤ ከተደረገላቸው እንደማንኛውም ጤነኛ ህጻን ንቁና ቀልጣፋ የመሆን ዕድላቸው የሰፋ ይሆናል።

በተለይ የሙያና የክህሎት ስልጠናዎችን በቀላሉ የመቀበልና የመተግበር ተሰጥኦ ያላቸው በመሆናቸው አምራች ዜጋ ሆነው ራሳቸውንና አገራቸውን የሚጠቅሙ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

በሌሎች አገራት የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች ፍላጎታቸውንና ተሰጦአቸውን በመለየት ስልጠናዎች የሚያገኙበት ዕድል ይመቻችላቸዋል ብለዋል።

በዚህም በተለያዩ የስራ መስኮች ከመሰማራት ባሻገር ለሌሎች የስራ እድል በመፍጠር ብቃታቸውን በማሳየት ለሌሎችም ዓርአያ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ራሱን የቻለ የስልጠናና የትምህርት ማዕከል ባለመቋቋሙ የችግሩ ተጎጂዎች የሆኑ ዜጎችና ወላጆች በእጅጉ እየተንገላቱ፣ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስም እየተዳረጉ መሆናቸውን አብራርተዋል።

መንግስት የትምህርት ተደራሽነትን ማሳካቱን ቢያሳውቅም የአዕምሮ እድገት ውስንነትን የሚያካትት ስርዓተ ትምህርትም ሆነ በቂ ማዕከላት አለመኖራቸውን ነው ምክትል ፕሬዝዳንቷ ያስታወቁት።

በመሆኑም በትምህርት ቤቶችና በሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት እነዚህን ዜጎች ያማከለ ስልጠናና ስርዓተ ትምህርት በመቅረጽ የትምህርት ተደራሽነቱ ሊረጋገጥላቸው ይገባል ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የአዕምሮ ውስንነት ቀን መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ስለ አዕምሮ እድገት ውስንነት ያላቸው ግንዛቤ እንዲዳብርና የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ንቅናቄ የሚደረግበት እንደሆነም አክለዋል።

በዓለም የጤና ድርጅት አሃዛዊ መረጃ መሰረት ከዓለም ሕዝብ ውስጥ ሶስት በመቶ የሚሆነው የአዕምሮ እድገት ውስንነት እንዳለበት ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም