ስፖርት ከጨዋታና ውድድርም በላይ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በመረዳት መስራት ይገባል

81

መጋቢት 17/2013/ኢዜአ/ ስፖርት ከጨዋታና ውድድርም በላይ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በመረዳት መስራት ይገባል ሲሉ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኖሙሳ ጃኮቢት ገለጹ።

የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌደሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ፣ የዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍና ሀገር አቀፍ ስፖርት ፌዴሬሽኖች የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኖሙሳ ጃኮቢት በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር ስፖርት  ከጨዋታና ውድድርም በላይ ዘርፉ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል።

ስፖርትን ለማሳደግ ደግሞ ተማሪዎች ላይ መስራት እንደሚገባና ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ውስጥ

ከጊዜው ጋር  እራስን እያበቁ መሄድ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው አፍሪካዊያን በጋራ የሚጋሯቸው የተለዩዩ ማንነቶችና እሴቶች እንዳሉ በመጥቀስ ከነዚህ መካከል ስፖርት አንደኛው መሆኑን ተናገራዋል።

አፍሪካ በጋራ ለመልማትና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ የ2063 አጀንዳ በመቅረጽ በጋራ ተጠቀሚ በሚያደርግ መልኩ በመስራት ላይ መሆናቸውን ምክትል ከንቲባዋ ተናገራዋል።

ለዚህ አጃንዳ እውን መሆን የጋራ ተጠቃሚነትን ባማከለ መልኩ በትብብር መስራት እንደሚገባም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ዩኒቨሲቲዎች ስፖርት ፌዴሬሽን ዓቃቢ ንዋይ አቶ አባይ በላይሁን፤ በኮቪድ-19  ምክንያት ከተጎዱት ዘርፎች መካከል ስፖርት አንዱ መሆኑን ጠቅስዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ በኮቪድ ምክንያት ጫና ውስጥ የገባውን ስፖርትን እንዴት መታደግ  እንደሚገባ ከሚነሱት ጉዳዮች መካከል መሆኑን ተናገራዋል።

ኢትዮጵያ ይህን መድረክ ለማዘጋጀት እድል በማግኘቷ ቱሪዝምን ለማሳደግና የሀገር ገጽታ ግንባታ ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።

ጉባኤው “የዩኒቨርስቲ ስፖርት ዓለምን ለመቀየር” በሚል መሪ ሃሳብ በኮተቤ ሜትሮፓሊታን ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት ነው የሚካሄደው።


በጉባኤው ላይ ከአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት የመጡ የስፖርት ፌዴሬሽን አመራሮችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም