ከመጀመሪያ ዙር መስኖ ልማት ከ270 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል--መምሪያው - ኢዜአ አማርኛ
ከመጀመሪያ ዙር መስኖ ልማት ከ270 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል--መምሪያው
ባህርዳር መጋቢት 16/2013 (ኢዜአ) በበጋው ወቅት በመጀመሪያው ዙር በመስኖ ከለማው መሬት ከ270 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርናና ገጠር ልማት መመሪያ አስታወቀ፡፡
በመምሪያው የመስኖና ፍራፍሬ ልማት አስተባባሪ አቶ ጌትነት ካሳሁን ለኢዜአ እንደገለጹት የዞኑን አርሶ አደር በበጋ መስኖ በማሳተፍ ተጨማሪ ሃብት ለመፍጠር እየተሰራ ይገኛል።
በበጋው ወቅት በመጀመሪያው ዙር የመስኖ ስራ ከ1ሺህ 400 በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 2 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት መልማቱን ተናግረዋል ።
በመስኖ ከለማው መሬት ከ270 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ገልጸዋል።
ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጎመንና ሌሎች የጓሮ አትክልቶች ጨምሮ በቆሎና ስንዴ በመስኖ ከለሙት መካከል ዋናዎቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።
በዘንድሮ በጋ አካባቢው ያለውን የውሃ ሃብትና የአየር ንብረት በመጠቀም ለመጀመሪያ ጊዜ 43 ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ የቆላ ስንዴ መልማቱን ተናግረዋል፡፡
በመተማ ወረዳ ወዲ የአንበሶ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር በለጠ አወቀ እንዳሉት ዘንደሮ በ4 ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት ቀይ ሽንኩርት ሽያጭ ከ200 ኩንታል በላይ ምርት አግኝተዋል።
ባለፈው ዓመት ያመረቱትን አንዱን ኪሎ ሽንኩርት በ13 ብር በመሸጥ 260 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል።
ዘንድሮ ዋጋው በመቀነሱ ገቢያቸው ይቀንሳል የሚል ስጋት እንደፈጠረባቸው አመልክተዋል።
በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በመስኖ ሁለት ሄክታር መሬት ማልማቱን የገለጸው ደግሞ ወጣት አርሶ አደር ዘመነ ድንቁ ነው።
በአንድ ሄክታር ላይ ቀይ ሽንኩርት እንዲሁም በቀሪው አንድ ሄክታር ላይ ደግሞ ቲማቲምና ቃሪያ ማልማቱን ገልጿል።
እስካሁን 60 ኩንታል የሸንኩርት ምርት ማግኘቱን ገልፆ አሁን ያለው የቀይ ሽንኩርት ዋጋ ዝቅተኛ በመሆኑ ያሰበውን ያክል ተጠቃሚ ባያደርገውም በቲማቲምና በቃሪያ ምርት ለማካካስ ተስፋ ማድረጉን ገልጻል።
በዞኑ ባለፈው ዓመት በመጀመሪያ ዙር በመስኖ ከለማው ከ1ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት ከ210 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱ ታውቋል።