2ኛው ዙር የኢንዱስትሪ ፓርኮች የንግድ ትርኢትና ባዛር በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

70

አዲስ አበባ መጋቢት 16/2013/ኢዜአ/ ሁለተኛው ዙር የኢንዱስትሪ ፓርኮች የንግድ ትርኢትና ባዛር በአዲስ አበባ ሊካሄድ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

የንግድ ትርኢትና ባዛሩ መጋቢት 17 ቀን 2013 ዓ.ም በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚካሄድ ሲሆን 31 የሚሆኑ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ይሳተፋሉ።

የኢንዱስተሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሁነቱን በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በኮርፖሬሽኑ የተወዳዳሪነትና ሥራ ፈጠራ ፕሮጀክት ስራአስኪያጅ አቶ ተሰማ ገዳ በሰጡት መግለጫ የንግድ ትርኢት እና ባዛሩ ዋነኛ ዓላማ የገበያ ትስስር መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኙ ድርጅቶች ከአገር ውስጥ አቅራቢዎች ጋር ትስስር ይፈጥሩበታልም ብለዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለማስተዋወቅና የኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪነት ለመጨመር እንደሚያግዝም ገልጸዋል።

የአገር ውስጥ ኢንተርፕራይዞች በኢንዱስተሪ ፓርኮች ከሚሰሩ ግዙፍ  ፋብሪካዎች ልምድ እንዲቀስሙ በማድረግ ለእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።

በንግድ ትርኢትና ባዛሩ ከንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዲሁም ከኢንዱስትሪ ፓርኮች የተወጣጡ ተወካዮች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የመጀመሪያው ዙር የኢንዱስትሪ ፓርኮች ንግድ ትርኢትና ባዛር ከየካቲት 3 እና 4 ቀን 2013 ዓ.ም በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ መካሄዱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም