የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽነሮች ጋር ተወያዩ

94

መጋቢት 16 / 2013 (ኢዜአ) የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ከአውሮፓ ህብረት የአለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ማዳም ጁታ ኡርፒላየን እና ከአውሮፓ ህብረት የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ሚስተር ጃነዝ ለናርሲስ ጋር ብራስልስ በኢትዮጰጵያና በህብረቱ መካከል ባሉ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል፡፡

ሚኒስትሩ መጪውን አገራዊ ምርጫን ጨምሮ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል፡፡

በተጨማሪም በትግራይ ክልል የሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦትንና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ እየተደረገ ስላለው ምርመራ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ወቅታዊ ሁኔታ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

የኢትዮ-አውሮፓ ህብረት የልማት ትብብርን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ለማድረግ እየወሰደ ላለው እርምጃ እውቅና እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት ባለሥልጣናት አክለውም ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት እና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ያላትን ቁልፍ ሚና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው መጠቆማቸውን በቤልጂየም የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ጠቁሟል፡፡

የአውሮፓ ህብረት እና የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የተጀመረው እ.አ.አ በ2016 ነው፡፡


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም