የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት ምክንያት ተጣርቶ በአፋጣኝ ለህዝብ ይፋ ይደረግ .... የአምቦና የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች

61
አምቦ/መተማ  ሀምሌ 22/2010 መንግስት የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞትን ትክክለኛ መንስኤን አጣርቶ በአፋጣኝ ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ የአምቦና የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋሪዎቹ እንዳሉት ለበርካታ ዓመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ታላቁን የህዳሴ ግድብ እውን ለማድረግ የአገር ባለውለታ የነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ህልፈተ ህይወታት መሪር ሀዘን ተሰምቷቸዋል፡፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት በኢንጂነር ስመኘው ላይ ጥቃት ያደረሱ አካላት ካሉ ፖሊስ በፍጥነት አጣርቶ ለህግ በማቅረብ ተገቢው እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነትን ሊያረጋግጥ ይገባል፡፡ በአገሪቷ ህዝቦች የተባበረ ክንድ ሥራው በመካሄድ ላይ ያለው ግድብ በኢንጂነሩ ሞት ሳይስተጓጎል በፍጥነት ተጠናቆ ለእሳቸው መታሰቢያ መሆን እንዳለበትም ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት፡፡ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የአቅማቸውን ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን የተናገሩት ነዋሪዎቹ፣ የልማት አርበኛው ኢንጂነር ስመኘው ዛሬ በሞት ቢለዩም ሥራቸው በታሪክ ደምቆ እንደሚጻፍ ገልጸዋል። ለግድቡ ድጋፋቸውን በማጠናከር የእርሳቸውን ውጥን ከዳር ለማድረስ አበክረው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል። በተመሳሳይ ዜና በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት ልባቸው ቢሰበርም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸው አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳውሃ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች ገልጸዋል። ኢዜአ  ያናጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት ድርጊቱ የኢትዮጵያን ልማትና ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎች የህዝብን ልብ ለመስበር የፈጸሙት ነው። በእዚህም የልማት ሀዋርያ የሆኑትን ኢንጂነር ስመኘውን ቢያጡም በእራሰቸው መሪነት ሲገነባ የነበረውን የህዳሴ ግድብ ለማጠናቀቅ በወኔና በቁጭት እንደሚነሱ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊትም በገንዘብና በጉልበት ሲያደርጉት የነበረውን ድጋፍ አጠናክረው ለመቀጠል መወሰናቸውን ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት። "ኢንጅነሩ በተለያዩ የግድብ ፕሮጀክቶች በመሳተፍ ለአገር ልማት ባለውለታ መሆናቸውን ገልጸው ለዓመታት የደከሙበት ልፋት ከንቱ እንዳይቀር መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለግድቡ ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ እንዲያጠናክርም ነዋሪዎቹ  ጠይቀዋል። መንግስት ለኢንጂነር ስመኘው ሞት ምክንያት የሆኑትን ፈጥኖ በመለየት ለህዝብ ይፋ ማድረግና ጥፋት የፈጸመ አካል ካለም ተገቢ እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ አለበት ሲሉም አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም