ሴቶች በፖለቲካ የመወሰን አቅማቸው እንዲያድግ በመጪው ምርጫ በንቃት መሳተፍ አለባቸው---ሴት ምሁራን

61

ደሴ መጋቢት 15 /7/2013(ኢዜአ) ሴቶች በሃገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የመወሰን አቅማቸውን ለማሳደግ በስድስተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ላይ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባቸው የወሎ ዩኒቨርስቲ ሴት ምሁራን ተናገሩ።

በዩኒቨርሲቲው የእንሰሳት ህክምና ኮሌጅ የቬተርናሪ ላብራቶሪ ቴክኖሎጅ ክፍል ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ገብረሚካኤል ለኢዜአ እንደገለጹት የሴቶችን ሁለተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በተግባር ለማረጋገጥ በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ሴቶች ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በየደረጃው ያሉ ሴቶች ከመራጮች ምዝገባ ጀምሮ ውጤቱ ይፋ እስኪደረግ ድረስ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ በባለቤትነት መሳተፍ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

አቅም ያላቸው ሴቶች እንዲመረጡ በመጠቆምና ድምጽ በመስጠት የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎና የውሳኔ ሰጭነት ሚና ለማሳደግ ወቅቱ አሁን እንደሆነ አመልክተዋል።

"ሴቶች ተፈጥሮ ያደላቸውን ጥበብና ብልሃት ተጠቅመው ለሀገራቸው የድርሻቸውን ማበርከት እንደሚጠበቅባቸውና አልችልም፤ ስራ ይበዛብኛል ከሚል የተሳሳተ አመለካከት መውጣት አለባቸው" ብለዋል።

እስካሁን የተደረጉ የይስሙላ ምርጫዎችም ሴቶችን ያገለሉ እንደነበሩ አውስተው ፤ የዘንድሮው እውተኛና ታአማኒ እንዲሆን ሴቶች በተደራጀ አግባብ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የእንሰሳት ህክምና ትምህርት ክፍል መምህርት ዶክተር ሰላማዊት ፈንታሁን በበኩላቸው ሴቶች ማህበራዊ ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተሳትፏቸው ከፍ እንዲል መንግስት የጀመራቸውን እንቅስቃሴዎች  ማጠናከር አለበት ብለዋል።

በተለይ በቀጣዩ ምርጫ እጩ ተመራጮችና መራጮች 50 በመቶ ሴቶች እንዲሆኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታችን እንዲወጡም  አሳስበዋል፡፡

ሴቶች ለሌብነት የማይመቹ፣ የመምራት ብቃትና ጥበብ ያላቸው መሆኑን፣ ለሀገር አንድነትና ሰላም የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ  ሁሉም ተገንዝቦ የሴቶችን ሁለተናዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

''ሴቶች ከባህል ተጽዕኖ ተላቀውና ድርብርብ ኃላፊነትን  ተቋቁመው መመረጥና መምረጥ እንዲችሉ ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ ይገባል'' ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህርት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሙሉ ወንድሙ ናቸው፡፡

ብልጽግናና  ተፎካካሪ ፓርቲዎችም የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ምቹ መደላድል መፍጠር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ የደቡብ ወሎ ዞን  ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን አሊ በሰጡት አስተያየት በዞኑ 13 በመቶ ብቻ የሆነውን የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ የሴቶች ተሳትፎ  50 በመቶ  እንዲሆን ለማስቻል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም