የቴክኖሎጂ ኮሙኒኬሽኑ ዘርፍ ከሕግ ማስከበር ዘመቻ እስከ ልማት ስራዎች ድረስ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

80

አዲስ አበባ መጋቢት 14 ቀን 2013 (ኢዜአ) የቴክኖሎጂ ኮሙኒኬሽኑን ዘርፍ ከሕግ ማስከበር ዘመቻ እስከ ልማት ስራዎች ድረስ ጥቅም ላይ በማዋል እየተሰራ እንደሚገኝ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።

5ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድና በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀርቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ እየሰጡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየሰጡት ባለው ማብራሪያ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ሰፊ ስራዎችን እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል፤ለአብነትም በሁለት አመት ውስጥ ኢትዮጵያ ሁለት ሳተላይት ወደ ህዋ መላኳን አመልክተዋል።

“የሰው አልባ በራሪ አካል (ድሮን) በመጠቀም ረገድ ለህግ ማስከበር ስራዎች ፣ ለአንበጣ መካላከያና የህክምና አቅርቦትን ለማዳረስ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል” ብለዋል።

በዚህም የኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂው ዘርፍ “ከጦርነት እስከ ልማት ባለው ስራ ውስጥ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስን በተመለከተ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በህክምናው ዘርፍ ሰፊ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስረድተው ቋንቋን በማስፋፋትና ወደ ሃብት ለመቀየር ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

ወንጀልን ለመከላከልም ሰፊ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ነው የተናገሩት።

ደመናን ወደ ዝናብ የሚቀይረው ቴክኖሎጂም በሚቀጥሉ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ተመርቆ ወደ ስራ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም