የአቶ ተስፋዬ ጌታቸው የቀብር ስነ-ሥርዓት ተፈጸመ

102
ባህር ዳር ሀምሌ 21/2010 የአቶ ተስፋዬ ጌታቸው የቀብር ስነ-ሥርዓት ዛሬ በባህርዳር  ከተማ አባይ ማዶ በሚገኘው ቅዱስ ገብርኤል ቤቴ ክርስቲያን ተፈፀመ። በቀድሞው የጎንደር ክፍለ ሀገር ጋይንት አውራጃ ስማዳ ወረዳ መጋቢት 21 ቀን 19 62 ዓ.ም.የተወለዱት አቶ ተስፋዬ ጌታቸው በሀገሪቱ ተፈጥሮ የነበረውን ህዝባዊ ጭቆና ለመታገል ከቀድሞው ኢህዴን ከአሁኑ ብአዴን ጋር ገና በልጅነት እድሜያቸውን ወደ ትግሉ ጎራ የተቀላቀሉት፡፡ በቀብር ስነሰርዓታቸው ወቅት በተነበበው የህይወት ታሪካቸው ላይ እንደተመለከተው  አቶ ተስፋዬ ጌታቸው በ1982 ዓ.ም. ትግል ከጀመሩበት አንስቶ ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ከወረዳ እስከ ክልል ድረስ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከኢትዮጰያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በልማት አስተዳደርና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ አሜሪካን  ከሚገኘው ፓስፊክ ዩኒቨርሲቲ በተቋም አመራር አግኝተዋል። የአቶ ተስፋዬ ጌታቸው አብሮ አደግና የትግል አጋር የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ  ዶክተር አምባቸው መኮንን በቀብር ስነ-ስርዓቱ ወቅት  እንደገለጹት አቶ አቶ ተስፋዬ  ከራሳቸው ይልቅ ለህዝብ ጥቅም የሚጨነቁና እንደ ክልልም እንደ ሀገርም ፍትሃዊ  ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት ሰጥተው ሰርተው አልፈዋል። አቶ ተስፋዬ ገና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ትግል ከተቀላቀሉበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ አላግባብ መበልጸግንና ኪራይ ሰብሳቢነትን አጥብቀው የሚዋጉ ንጹህ የህዝብ ልጅ ነበሩ። " ለህዝብ ጥቅም ሲሉ እስከ እለተ ሞታቸው ድረስ የታገሉለት ዓላማ እንዳይቀለበስ ወጣቶች ዓላማቸውን በማንገብ በርትተው መስራት ይኖርባቸዋል"  ሲሉ ሚኒስትሩ አሳስበዋል። አቶ ተስፋዬ ከ1988ዓ.ም.  እስከ 1989 ዓ.ም. የደቡብ ጎንደር አስተዳደር ዞን አቅም ግንባታ ኃላፊ፣ የዞኑ ስራ አስፈጻሚ አባልና የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ኃላፊ በመሆን ሰርተዋል። ከ1994 ዓም ጀምሮ በነበራቸው የአፈጻጸም ብቃትና ህዝባዊ ወገንተኘነት  ወደ ክልል እንዲመጡ ተደርጎ በተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች ላይ ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ከነዚህም ከሰሩባቸው መካከል የአማራ ክልል የጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ኢንዱስትሪ ስራዎች ማስፋፊያ ስራ አስኪያጅ፣ የአማራ ክልል ንግድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ በመሆን ማገልገላቸው ተጠቅሷል። ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ ንግድ፣ኢንዱስትሪና የገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊና ከሚያዚያ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ህይወታቸው እስካለፈችበት ቀን ድረስ  በምክትል ርዕሰ መስተዳደር የርዕሰ መስተዳደሩ የህዝብ ግንኙነትና አደረጃጀት አማካሪ እንዲሁም  የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ሰርተዋል። አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ባጋጠማቸው ህመም በውጪና በሀገር ውስጥ ህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ48 ዓመታቸው ሐምሌ 18/2010 ዓ.ም. ለህክምና አሜሪካ እንዳሉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። በቀብር ስነስርዓታቸው ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መከንን፣የኢፊዲሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራልና የተለያዩ ክልሎች  የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ባለትዳርና የሦሰት ወንድ ልጆችና የአንድ ሴት ልጅ አባት ነበሩ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም