የኢንጂነር ስመኘው አስከሬን በመስቀል አደባባይ የሽኝት ፕሮግራም በመዘጋጀቱ ሁሉም ተገኝቶ ሃዘኑን መግለጽ ይችላል

121
አዲስ አበባ  ሀምሌ 21/2010 የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጅነር ስመኘው አስከሬን የሽኝት ፕሮግራም በመስቀል አደባባይ ነገ በመዘጋጀቱ ሁሉም ተገኝቶ ሃዘኑን በመግለጽ መሸኘት እንደሚችል ተገልጿል። የኢንጅነር ስመኘው በቀለ አስከሬን ለምርምራ ከተላከበት ከጳውሎስ ሆስፒታል ዛሬ ከሰዓት በኋላ ወደ መኖሪያ ቤት ሽኝት ተደርጎለታል። በሽኝቱ ከሆስፒታሉ ጀምሮ እስከ መኖሪያ ቤት ድረስ  ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ነዋሪዎች በመገኘት ሃዘናቸውን ገልጸዋል። የኢንጀነር ስመኘው በቀለ የቀብር ስነስርዓት በነገው እለት  በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴደራል ከቀኑ በሰባት ሰዓት እንደሚፈጸም በብሔራዊ የቀብር አስፈጻሚው ኮሚቴ ስም የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ ገልጸዋል። ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ ከጠዋቱ አራት ሰዓት ተኩል ጀምሮ በመስቀል አደባባይ ልዩ የሽኝት ፕሮግራም ስለተዘጋጀ ማንኛውም ሰው በመገኘት ሃዘኑን መግለጽ እንደሚችል ተናግረዋል። ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ባከናወኗቸው የልማት ተግባራት ዘላለም በክብር ሲታወሱ እንደሚኖሩ የገለጹት ሚኒስትሩ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ከዳር በማድረስ ለኢንጂነር ስመኘው ያለንን ክብርና ፍቅር ማሳየት ይገባልም ብለዋል። ሚንሰትሩ በቀብር ስነስርዓቱ ላይም የአዲስ አበባ ነዋሪ መንገዶችን ክፈት በማድረግ የተለመደ ትብብሩን እንዲያሳይ በቀብር አስፈጻሚው አብይ ኮሚቴ  ጠይቀዋል። በሽኝቱ ስነስርዓት የተገኙት የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ እንደገለጹት፤ ኢንጅነር ስመኘው 'ደከመኝ ሰለቸኝ' ሳይሉ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ከጅማሮ አንስቶ ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ሲመሩ ቆይተዋል። ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ ም በመስቀል አደባባይ መኪናቸው ውስጥ ሞተው የተገኙት ኢንጂነር ስመኘው አስከሬን ምርመራ ተጠናቆ ወደ መኖሪያ ቤታቸው በክብር መሸኘቱን ገልጸዋል። ኢንጂነር ስመኘው በቀለ መስከረም 3 ቀን 1957 ዓ.ም በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ልዩ ስሙ ማክሰኝት በተባለ ቦታ ነው የተወለዱት። ከ1978 እስከ 1991 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ኮተቤ በሚገኘው ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አገልግለዋል። ከ1991 እስከ 1992 በኢንጂነሪንግ ክፍል በሲቪል ምህንድስና ሰርተዋል። ከ1997 እስከ 2002 ዓ.ም ባለው ጊዜ ደግሞ በግልገል ጊቤ ፕሮጀክት ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን የግልገል ጊቤ ሁለት ዋና ስራ አስኪያጅ በመሆን ሰርተዋል። ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ የኢትዮዽያዊያን የድካም ውጤትና ተስፋ በሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም