ዘመኑን የዋጀ የመንግስት አገልግሎት ለመስጠት የፖሊሲው መሻሻል ወሳኝ ሚና ይጫወታል

102

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11/2013(ኢዜአ) ዘመኑን የዋጀ የመንግስት አገልግሎት ለመስጠት የፖሊሲው መሻሻል ወሳኝ ሚና እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ተናገሩ።

ተግባራዊ ከተደረገ ሁለት አስርት ዓመታትን ያስቆጠረው የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ፖሊሲ ላይ ማሻሻያ ማድረግ የሚያስችል ጥናት ተካሂዷል።

ጥናቱን የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በጋራ አካሂደውታል።

በጥናቱ ረቂቅ ላይ ከሁሉም ክልሎችና ከአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ሃላፊዎችና የሚመለከታቸው አካላት ተወያይተውበታል።

የጥናቱ ተሳታፊዎች የሆኑት ዶክተር አለማየሁ ደበበና ፕሮፌሰር ሳምሶን ካሳሁን  አገልግሎቱን ለማሻሻል የአገልግሎት ሰጪው ቅንነትና ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ በየጊዜው በሚሻሻል ፖሊሲ ሊመራ እንደሚገባም አመላክተዋል።

በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ላይ ከፍጥነት፣ ቅልጥፍናና ጥራት ባለፈ በቂ መረጃ አለማግኘት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግርና ተገልጋይን በአክብሮት አለማስተናገድ በስፋት እንደሚስተዋሉ በጥናቱ ተገልጿል።

በየተቋማቱ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች የተለያዩ ቢሆኑም ችግሮቹ ግን በሁሉም ላይ የሚስተዋሉ መሆኑም እንዲሁ።

አገልግሎትን ማቀላጠፍ የመንግስትን ወጪ ከመቀነስ ባለፈ የህዝብ እርካታን መጨመርና የአገሪቷን ዕድገት ማፋጠን እንዲሁም ኢንቨስትመንትን ማበረታታት መሆኑም ተነስቷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በየክልላቸው ያለው የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ዜጎች ተደጋጋሚ ቅሬታ እንደሚያነሱ አልሸሸጉም።

ችግሩን ለመፍታት በተለይ በርካታ ተገልጋይ ያለባቸውን ዘርፎች በመለየት በአጭር ጊዜ ለመፍታት እርምጃ መጀመራቸውንም አንስተዋል።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር በዛብህ  ገብረየስ ዜጎች የመንግስት አገልግሎትን ፈጣንና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ የማግኘት መብት ቢኖራቸውም ቢሮክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ማነቆ ሆኖባቸዋል ብለዋል።

ነጻ፣ ገለልተኛና በራሱ መፈጸም የሚችል ሲቪል ሰርቪስ አለመኖሩ ቀደም ሲል ተግባራዊ ተደርጎ የነበረው ፖሊሲ ውጤታማ እንዳይሆን ማድረጉንም ተናግረዋል።

የሚሻሻለው ፖሊሲ ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮችን በአግባቡ ፈትሾ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት የሚያስችል እንዲሆን ይጠበቃል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የመንግስት ሠራተኞች መኖራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም