የባከነ ኃብት...!

68
 አዋድ አብዱልሰቡር (ኢዜአ) በአሜሪካ ታሪክ ሁነኛ ስፍራ ከሚቸራቸው የፖለቲካ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው - 35ኛው የአገሪቷ ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ፡፡ ለአገራቸው ብዙ መስራት በሚችሉበት ወጣትነት እድሜያቸው በሰው እጅ ሕይወታቸውን ያጡት እኚህ ሰው በፖለቲካ ንግግራቸው ያስተላልፏቸው በነበሩት ጠንካራና ወርቃማ መልዕክታቸው ዝንት ዓለም ይወሳሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ግን በአውሮፓዊያን አቆጣጠር 1961 በተካሄደው ፕሬዚዳታዊ ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ በተከናወነው በዓለ ሲመታቸው ባስተላለፉት መልዕክት የጠቀሷት አጭር፤ በሀሳብ ደረጃ ግን እጅግ ግዙፍ የምትባል ዓረፍተ ነገር ዘመን ተሻግራ አሁንም ድረስ የምትወሳ ናት፡፡ “ውድ አሜሪካዊ ወገኔ፤ አገርህ  እንድታደርግልህ የምትሻውን ከመጠየቅ ይልቅ አገሬ ከእኔ ምን ትሻለች የሚለውን አስቀድም” የሚለው አባባላቸው የብዙዎችን ስሜት የገዛች፤ ወደፊት የምትገዛ ናት። የተለያዩ አካላት ለዚህ የኬነዲ የፖለቲካ ንግግር የጋራ የሆነ ትርጓሜ ይሰጣሉ፡፡ መልዕክቱ የዜጎች ህልም እውን የሚሆነው የስልጣን እርካቡን በተቆናጠጡ መሪዎች ሳይሆን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ባለው ህዝብ ትጋትና ቁርጠኝነት መሆኑን ይገልፃል፡፡ እኒህ የኬኔዲ ቃላት የሚነግሩን ቁም ነገር የለውጥ ጎዳናው ፊት አውራሪ መሪዎች ቢሆኑም ያለዜጎች መስዋእትነት የሚታለመው ህልም ከቶውንም ሊጨበጥ የማይችል ከንቱ ድካም መሆኑንም ጭምር ነው፡፡ በመሆኑም የአገሮች ልማትም ሆነ ጥፋት የሚወሰነው በራሳቸው በዜጎች ምርጫ ስለመሆኑ እንድናጤንም እነዚህ ቃላት ይጠቁሙናል። መልዕክቱ በአሜሪካ የጊዜው የፖለቲካ ኢኮኖሚ አውድ (CONTEXT) ጋር ተያይዞ በጊዜው ለነበረው ትውልድ የተላለፈ ቢሆንም በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ከአሜሪካ አልፎ በሌሎች የዓለም ህዝቦች ዘንድም መነቃቃትን የፈጠረ፤ ዘመን እየተሻገረም እያገለገለ ያለ ወርቃማ የፖለቲካ ንግግር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አዲስ የለውጥ ጎዳና መሰረት እየተጣለ ነው፡፡ “መደመር” በሚል መርህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ እና ባልደረቦቻቸው የተጀመረው ይህ የለውጥ ጎዳና መልካም የሚባል አገራዊ እና ህዝባዊ ድባብ ፈጥሯል። የለውጥ ሂደቱ የመጨረሻ ግብ ደግሞ ፍትህ የነገሰባት፣ ሰላሟ የተረጋገጠ እና  የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ነው። እንዲህ ዓይነቷን “ኢትዮጵያ ማየት የማይሻ ሊኖር ይችላል” ብሎ ማሰብ ያዳግታል። ይህች ኢትዮጵያ  የሁሉም ዜጋ የዘወትር ህልም፣ ምኞትና ጉጉት ናት። ይህችን ኢትዮጵያ ለማየት “የሁሉንም አንድነትና ህብረት ያሻል” በሚል ሀሳብ  ለመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ የብዙሃኑን ድጋፍ እያገኙ ያለውም ለዚህ ነው። በከፍተኛ መጠንና ትጋት የተቃውሞ ፖለቲካ ሲያራምዱ የቆዩ ፤ ፍፁም ፅንፍ ይዘው ዘመናትን ያሳለፉ ኃይላት ሳይቀሩ ለአዲሱ የለውጥ ሂደት ሞተር ለመሆን ጦራቸውን ጥለው ወደአገር ቤት እየተመለሱ ያለውም እንዲሁ። ኢትዮጵያዊያን ተቆጥረው የማያልቁ የፖለቲካ እና የምጣኔ ኃብት ጥያቄዎች ያሏቸው ቢሆንም እነዚህ ጥያቄዎች ተመልሰው ሁሉም የሚሻትን ውብ አገር ማምጣት የሚቻለው ግን በቅድሚያ ሁሉም በየግሉ የአቅሙን  አስተዋፅኦ ሲያበረክት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከአገር አልፎ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ድረስ ያጋቡት ይህ የድጋፍ ነውጥ ወደሚታይና የሚጨበጥ ልማት እንዲሻገር በየአጋጣሚው ጥሪ የሚያቀርቡትም ለዚህ ነው። እርሳቸው እንደሚሉት አገር የሚገነባው በመንግስታት ሳይሆን በዜጎች ነው። ከእነዚህ መካከል በተለያዩ የውጭ አገሮች የሚኖሩ ዜጎች (ዲያስፖራዎች) ዓይነተኛ የእድገት መሳሪያዎች ናቸው። ለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል። ባለፈው የአውሮፓዊያኑ ዓመት የወጣ አንድ ሪፖርት በውጭ አገሮች የሚኖሩ አፍሪካዊያን በየዓመቱ ከአንድ መቶ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ወደአገሮቻቸው ይልካሉ። በቁጠባ መልክና ለወዳጅ ዘመድ ተብሎ በየአገሮቻቸው ባንኮች በኩል የሚያልፈው ይህ ሀብት በአግባቡ ሥራ ላይ የሚውልበት ስርዓት ቢበጅ በአህጉሪቷ በየዓመቱ ለመሰረተ ልማት አውታሮች ግንባታ የሚያስፈልገውን የፋይናንስ ምንጭ በብቃት ለማሟላት የሚያስችል ነው። በውጭ ከሚኖሩ የአፍሪካ አገሮች ዜጎች የሚሰበሰበው ይህ ኃብት አገራቱ ከቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ከሚያገኙት ገቢ በእጅጉ የበለጠ መሆኑንም ሪፖርቱ ይጠቁማል። በዚህ ረገድ  በዋነኝነት የምትጠቀሰው አገር ሰሜን አፍሪካዋ ግብፅ ናት። ባለፈው የበጀት ዓመት ብቻ ግብፃውያን ከ16 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወደአገር ቤት ልከዋል። ግብፃውያኑ በውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ቤት የሚልኩት ይህ ገንዘብ የአገሪቷን ዓመታዊ የወጪ ንግድ ገቢ 72 በመቶ ይሸፍናል። የአገሪቷን ዓመታዊ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት መጠን ደግሞ በአራት እጥፍ ይበልጣል። ይህ ሁኔታ ናይጄሪያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የሚያበረታታ ቢሆንም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለው ልምድ ግን ደካማ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተለያዩ “የዓለም ክፍሎች ይኖራሉ” ተብለው ከሚገመቱት ሶስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን መካከል በመደበኛው ህጋዊ መንገድ ወደአገር ቤት ገንዘብ የሚልኩት 22 በመቶ ያህሎቹ ብቻ ናቸው። ባለፈው የአውሮፓዊያን ዓመት በወጣ አንድ ዘገባ በእነዚህ ኢትዮጵያዊያን በባንኮች በኩል ወደአገር ቤት የተላከው የውጭ ምንዛሪ መጠን አራት ቢሊዮን ዶላር ያህል ብቻ ነው። ሁሉም ለአዲሱ የለውጥ ጅማሮ እየሰጠ ያለውን ድጋፍ ትርጉም ወዳለውና ወደሚጨበጥ አስተዋፅኦ መለወጥ ይጠበቅበታል የሚባለው ለውጡ ጠንካራ መሰረት ላይ እንዲገነባ የዜጎችን መስዋእትነት ፣ የእለት ተዕለት ትጋት እና ከራስ ይልቅ ለሌሎች ደህንነት መቆምን የግድ ስለሚሻ ነው።  ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያለው ኢትዮጵያዊ  በሚችለው አቅም ሁሉ የሚችለውን አስተዋፅኦ ማበርከት ከተሳነው ቃላዊ ድጋፍ እየተቸረው ያለው የለውጥ ሂደት የትም አያደረሰም። ከዚህ አኳያ “ትልቅ ሚና ይጫወታሉ” ተብለው እምነት ከሚጣልባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል በውጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ግንባር ቀደም ናቸው። ለብዙ ዘመናት ኑሯቸውን በውጭ ያደረጉት እነዚህ ወገኖች በእውቀታቸውና በኃብታቸው አገራቸውን ለማገልገል የሚያስችል አቅም ያካበቱ ናቸው። ሆኖም ግን ይህንን አቅማቸውን ለአገራቸው እና ድሃ ወገናቸው ለማዋል የሚያደርጉት ጥረት እጅግ ዝቅተኛ ስለመሆኑ እላይ የተጠቀሰው አሃዛዊ መረጃ በቂ ነው። ብዙዎች የሚያቀርቡት ዋናው ምክንያት በአገሪቷ ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች ያለፉት የፖለቲካ አስተዳደሮች ይህን ለመሰለው ተግባር አመቺ አለመሆናቸውን ነው። ይህ ምክንያት በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ እውነትነት ሊኖረው ይችል ይሆናል። ሆኖም ግን ግብፃውያንም ሆኑ ለህዝቦቻቸው ጥቅም ሲሉ የሚቻላቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ ያሉ የአፍሪካና የሌሎች ዓለም አገሮች ዲያስፖራዎች ተመሳሳይ የፖለቲካና ምጣኔ ኃብታዊ ፈተናዎች ሳይኖሩባቸው ቀርቶ አለመሆኑንም ማጤን ይገባል። የእነዚህ አገሮች ዲያስፖራዎች እየሰሩ አገራቸውንና ወገናቸውን ከመርዳት  አልተቆጠቡም። ይህ ተግባራቸው ለዘመናት የኖረ ባህላቸው በመሆኑ ምንም ዓይነት ሌላ ቅድመ ሁኔታም ሆነ ስሌት ውስጥ አይገቡም። ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳትም ይሁን ከሚያገኙት ለመቆጠብ የሚሹትን ገንዘብ ወደአገር ቤት ይልካሉ። ምንም ይሁን ምን የመጨረሻ ዞሮ መግቢያ ቤታቸው አገር መሆኗን በቅጡ በመገንዘባቸውም ድልድዩን ሳይሰብሩ እትብቱን ሳይቆርጡ ይዘልቃሉ። በዚህም “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንዲሉ ራሳቸውንም ወገናቸውንም ይጠቅማሉ። በእኛ ዘንድ ግን ይህ ታላቅ አገራዊ ኃብት ባክኗል። ይህ የሆነው ግን ኢትዮጵያውያኑ የሚጠበቅባቸውን አገራዊ ግዴታ የመወጣትና ወገኖቻቸውን የመርዳት ፍላጎት አጥተው ነው ከሚል እምነት አይደለም። የአገራቸውንና ወገናቸውን ውለታ በመዘንጋት ነው ለማለትም ያዳግታል። የመዘናጋቱ ምንጭ ከተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰብ ትርጓሜዎች ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ “ብዥታዎች ሳቢያ ነው” ብሎ መገመት ይቻላል። የሆነው ሆኖ አሁንም አልዘገየንም። የባከነውን በማካካስ ጭምር ኃላፊነታችንን ለመወጣት የሚያስችሉ ሰፊ እድሎች ከፊታችን አሉ። እነዚህን አመቺ እድሎች የተገነዘቡ በውጭ የሚኖሩ ዜጎቻችን ከወዲሁ ፊታቸውን ወደእናት አገራቸውና ድሃ ወገናቸው ማዞር ጀምረዋል። ኢትዮጵያዊያን የዲያስፖራ አካላት በተለይም በአሜሪካ የሚኖሩ አያሌዎች የለውጥ ጎዳናው አካል ለመሆን ዝግጁነታቸውን እያሳዩ ናቸው። በአሜሪካ ተፅእኖ ፈጣሪ የሚባሉ አካላትን ጨምሮ የተለያዩ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት ስብሰባ ጠርተው በአገራቸው የሚካሄደው ለውጥ አካል ለመሆን ቆርጠው መነሳታቸውን አረጋግጠዋል። በፍጥነት እየነጎደ ባለው የለውጥ ባቡር በመሳፈር የሚጠበቅበትን አገራዊ ኃላፊነት እንዲወጣ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች በየግላቸው መጠራራት ጀምረዋል። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በውጭ የሚኖሩ ዜጎች አገር ቤት ለሚገኙት ዘመድ ወዳጆቻቸው በውጭ ምንዛሪ የሚልኩትን ገንዘብ በህጋዊ መንገድ በባንኮች በኩል እንዳይልኩ ይደረግ የነበረውን ቅስቀሳም አቁመዋል። በዚህ መልካም ምላሽ የተበረታታው የኢትዮጵያ መንግስትም በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን አገራዊ ተሳትፎ ለማጠናከር የሚያስችል አንድ እርምጃ በቅርቡ ወስዷል። ኢትዮጵያውያን የለውጥ ጉዞውን የሚደግፉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት “የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ” እንዲቋቋም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሀሳብ መሰረት ፈንዱ ተቋቁሟል። በተለያየ መልክና ቅርፅ የሚቋቋሙ ትረስት ፈንዶች በተለይ ድህነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለል ለሚደረጉ የልማት ጥረቶች ዓይነተኛ የገንዘብ ምንጭ ናቸው። ትረስት ፈንድ ግለሰቦችንና የግል ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሚመቻቸው መንገድ በሚሰጡት ልግስና የሚንቀሳቀስ አካል ነው። ፈንዱም ትምህርትንና ጤናን ጨምሮ ድህነት ተኮር ለሆኑ የልማት ተግባራት ሊውል ይችላል። ሶስት ሚሊዮን የሚገመተውን ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ የአገሩ ጉዳይ ባለቤት ለማድረግ ከሚያስችሉ ስልቶች መካከል አንዱ የዚህ ዓይነቱ የማህበረሰብ ፈንድ ነው። በዚህ መንገድ  ይህንን የህብረተሰብ ክፍል በስፋት እና በብቃት ማነቃነቅ ከተቻለ የማይተካ ሚና የሚኖረው የአገር ኃብት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ታዛቢዎች ይገልፃሉ። ፈንዱ ነፃና ገለልተኛ በሆነ ስርዓት ተግባሩን በመከወን የታለመለትን ግብ እንዲመታ የሚያስችለው ተቋማዊ አደረጃጀት ይፈጠርለታል ተብሏል። ፈንዱ ራሱን ችሎ በሚቋቋም ተቋም አማካኝነት የሚተዳደርና በቦርድ የሚመራ እንደሆነም ተመልክቷል። ትልቅ ስፍራ የተሰጠውን ይህን ፈንድ ጨምሮ የዲያስፖራው ማህበረሰብ በአገሩ ጉዳይ የሚያደርገው ተሳትፎ  አገሪቷ ለምታልማቸው ዘላቂ ልማቶች “ወሳኝ ናቸው” ብላ እየተጋችላቸው ካሉት የወጪ ንግድ እና ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት በላቀ ሁነኛ የአገር አለኝታ መሆን የሚችል ነው። ይህ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር እያካሄዱ ባለው ውይይት ላይ አንዱ አንኳር አጀንዳ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል። ዲያስፖራው በአገሪቷ ሁለተናዊ  እንቅስቃሴ ውስጥ በሚገባው መጠን ይሳተፍ ዘንድ ሊቀየሱ የሚገባቸውን ስልቶችም የውይይቱ መነጋገሪያዎች መሆን እንዳለባቸው ይታመናል። በዚህ ረገድ ከዚህ በፊት የተወሰዱና የመከኑ ስልቶች መደገም የለባቸውም። በኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራ ማህበረሰብና መንግስት መካከል አሁን የተፈጠረው የመተማመንና የመተጋገዘ መንፈስ በተለይ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው ነው።  ከፊታችን ቅዳሜ ሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለሶሰት ቀናት የሚቆየው ይህ ውይይት "የጥላቻና የልዩነት ግንብን አፍርሰን የይቅርታና የፍቅርን ድልድይ እንገንባ" በሚል መሪ ሀሳብ የተሰየመውም ለዚህ ሳይሆን አይቀርም። ይህ አጋጣሚ የሀብት ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሚደመሩ እሴቶች አሉት ከሚባለው ማህበረሰብ  ጋር የሚደረገው ውይይት በቴክኖሎጂና ዕውቀት ሽግግር፣ በኢንቨስትመንት፣ በውጭ ዓለም አገርን በማስተዋወቀና ሌሎች አገራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራል ተብሎም ይታሰባል። በዚህ ሂደት ታዲያ “እንዲህ ይደረግልኝ ሳይሆን ምን ላድርግ  የሚለው ጥያቄ ከምንም በላይ ክብደት ሊሰጠው ይገባል” የሚለው የብዙዎች ተስፋ ነው።  ለዚሀ ዓይነቱ አስተሳሰብ ቅድሚያ ከተሰጠ ሌላው በራሱ ጊዜ ተከታትሎ ይመጣል የሚለው እምነት በሁሉም ዘንድ ሊጎለብት ይገባል። የሆነው ሆኖ ግን አሁን ላይ የዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ፍንጭ ከወዲሁ ብቅ ማለት ይዟል። በርካታ ኢትዮጵያዊያን ከወዲሁ  የትረስት ፈንዱ አካል መሆን ጀምረዋል። መንግስት በፈንዱ ስም ወደከፈተው የባንክ ሂሳብ ገንዘብ ማስገባትም ጀምረዋል። ይህም ለለውጡ እየሰጠ ያለውን ቃላዊ ድጋፍ በተጨባጭ በተግባር እየተረጎመ መሆኑን ያሳያል። “አገርህ  እንድታደርግልህ የምትሻውን ከመጠየቅ ይልቅ አገሬ ከእኔ ምን ትሻለች ብለህ ጠይቅ” የሚለው ግማሽ ምዕተ ዓመት አልፎ አሁንም ድረስ የብዙዎች ብርታት የሆነው የጆን ኤፍ ኬኔዲ ፍልስፍና በመላው ኢትዮጵያውያን ዜጎች በተለይም በወጣቱ ዘንድ ጠልቆ ሊገባና ሊነግስ ግድ ይላል። ኢትዮጵያውያን አሁን እየዘመርንለት ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የ“መደመር” መርህ ግቡን ከመታ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያመረቃ ለውጥ እንደሚያመጣ ጠቅላያችን በአንደበታቸው ነግረውናል። በተለይ ኢትዮጵያዊያን የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ብዙ ሳይቸገሩ በሚያበረክቱት አስተዋፅኦ የሚሊዮኖች ድሃ ወገኖቻቸውን ህይወት በቀላል መታደግ ይችላሉ። ይህንን ለመተግበር ደግሞ አሁን የተፈጠረላቸው እድል ከመቼውም ጊዜ የላቀ ነው።  የጥላቻና የልዩነት ግንቡ ፈርሷል። ላለፉት በርካታ ዓመታት ያለአግባብ የባከነው የአገር አለኝታ ለሚሊዮኖች ሕይወት ሊሆን፣ ተስፋ ሊዘራ ደጅ ላይ ደርሷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም