የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ጥረት ኅብረተሰቡም ሊደግፍ ይገባል

85

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11/2013(ኢዜአ) የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት ኀብረተሰቡም ሊደግፍ እንደሚገባ ተገለፀ።

"የሴቶችን መብት የሚያከብር ማኀበረሰብ እንገንባ" በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ የሚገኘውን የሴቶች ወር አስመልክቶ በሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የተዘጋጀ 'የገጠሯ ሴት የቀን ውሎ' የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ለእይታ ቀርቧል።

የ50 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው ዘጋቢ ፊልሙ በ10ሩ የአገሪቷ ክልሎች የሚገኙ ሴቶችን የቀን ውሎና የኑሮ ውጣ ውረድ የሚያስቃኝ ነው።

በዘጋቢ ፊልሙ ታሪካቸውን ያጋሩት አብዛኞቹ ሴቶች ኑሯቸውን ለመግፋት የንፁህ መጠጥ ውሃና የኤሌክትሪክ አገልግሎት አለመሟላት ፈተና እንደሆነባቸው ይተርካሉ።

ተራኪዎቹ እናቶች በፈተና ውስጥም ሆነው ነገን ለማሳመር ተስፋ ሰንቀው ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ይልካሉ፤ ነገ የተሻለ እንደሚሆን ያምናሉ፤ ችግራቸው እንዲፈታላቸውም ይጠይቃሉ።

በመድረኩ ላይ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትሯ ፊልሰን አብዱላሂ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲና ሌሎችም የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሴት ካፒቴኖችና ሰራተኞች፣ ሴት የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ ሴቶችም እንዲሁ።

ሚንስትሯ ፊልሰን አብዱላሂ በአገሪቷ በድህነት ውስጥ የሚገኙ ሴቶች የተሻለ ህይወት እንዲኖሩ ለማድረግ ሁሉም ሊሰራ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በዘጋቢ ፊልሙ የተቃኘውን የሴቶች ችግር ለመፍታት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አይነተኛ ሚና ስላለው ለግድቡ መጠናቀቅ የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።

የሴቶችን ችግር ለመፍታት የትምህርት ፋይዳም ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው አገሪቷ ያላትን ሀብት መጠቀም ከተቻለና እርስ በእርስ መተባበር ካለ ታሪክ መስራት እንደሚቻል ተናግረዋል።

የእነዚህን እናቶች ህይወት ለመቀየር ከሃሳብ ጀምሮ ማንኛውንም ድጋፍ ማድረግ የሚሻ ሁሉ ሚኒስቴሩን ማናገር እንደሚችልም ገልፀዋል።  

ዘጋቢ ፊልሙ በ10 ክልሎች የሚገኙ የገጠር ሴቶችን ውሎ የሚያስቃኝ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ ናቸው።

ወሩ የሴቶች ወር ተብሎ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ መሆኑን ገልፀው የተያዘው ሳምንት የሴቶችን በኢኮኖሚ ማብቃት ላይ አተኩሮ እየተከበረ መሆኑን አንስተዋል።

የሴቶችን የስራ ጫና የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎች በማቅረብ በኩል ሚኒስቴሩ ሲሰራ መቆየቱንና አሁንም መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያከናወነ ያለውን ተግባር ሁሉም ሊደግፍ እንደሚገባም አሳስበዋል።

መንግስት የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት ኀብረተሰቡም እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል።

የኀብረተሰቡን አመለካከት ለመቀየር የተከናወኑ ተግባራት ለውጥ እንዳመጡ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ አሁንም የሰዎችን እኩልነት ያከበረ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የተጠናከረ ስራ ይጠይቃል ነው ያሉት።

በመድረኩ የተገኙ አስተያየት ሰጪዎችም በዘጋቢ ፊልሙ የታየውን የሴቶች ችግር ለመፍታት ሁሉም የመፍትሄ አካል ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።

ወንዶች ብቻቸውን የሚቀይሩት አገርና ዓለም የለምና ለሴቶች ችግር መፍትሄ ለመስጠት ሁሉም ሊረባረብ ይገባልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም