በሀገር ላይ የሚቃጣውን ጥቃት ለመመከት ወጣቱ የዜግነት ግዴታውን መወጣት እንዳለበት ተመለከተ

73

ዲላ መጋቢት 08/2013(ኢዜአ) በሀገር ላይ የሚቃጣውን ጥቃት ለመመከት ወጣቱ ትውልድ የመከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል የዜግነት ግዴታውን መወጣት እንዳለበት ተመለከተ።

በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ማህበር ጉባኤ በይርጋጨፈ ከተማ ባካሄደበት ወቅት የማህበሩ ሰብሳቢ ሻለቃ አረጋኸኝ አሰፋ ለሀገር የከፈለውን መስዋትነት ግምት ውስጥ ሳይገባ የተበተነው ሰራዊት ለችግር ተጋልጦ ቆይቷል ብለዋል።

ይህን ችግሩን ለመፍታትም ማህበር መስርተው  ከመንግስት ጋር በመተባበር እየሰሩ መሆናቸውን  ተናግረዋል።

የሀገሪቱን ሠላም ለማስከበር መስዋዕትነትን የከፈለ ወታደር ያለአግባብ ተባሮ ለችግር ተጋልጦ መታየቱ በአሁኑ ወቅት ወጣቱ መከላከያ ሰራዊቱን ተቀላቅሎ ለሀገሩ የሚጠበቅበትን እንዳይወጣ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቅሰዋል።

ሆኖም ለሀገር የሚከፈል ዋጋ ክብር መሆኑን ወጣቱ ተገንዝቦ በኢትዮጵያ ሉአላዊነት ላይ የሚቃጣ ማንኛውም ጥቃት ለመመከት የመከላከያ ሰራዊቱን ተቀላቅሎ የዜግነት ግዴታውን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።

የማህበሩ አባል ወታደር ተፈሪ ጤሮ በበኩላቸው በኛ ላይ የተፈጸመው አሁን ለሀገሩ ትልቅ መስዋዕትነት እየከፈለ ባለው ሰራዊት ላይ እንዳይደገም ወጣቱ የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል።

በእሳቸውም በኩል የሀገሪቱን ሠላም ለማደፍረስ በውስጥም ሆነ ውጭ የሚንቀሳቀሱ የጠላት ሃይል ለመመከት አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

መንግስት ለዓመታት ተዘንግቶ የቆየውን የቀድሞ መከላከያ ሰራዊት ችግሮች ለመፍታት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

ወጣቱም ትውልድ ለጸረ ሰላም ሃይሎች ተላላኪ ባለመሆን ሀገሪቱ ከተጋረጠባትን ስጋት ለማውጣት መነሳት እንዳለበትም አመልክተዋል።

ሌላው የማህበሩ አባል አስር አለቃ ምትኩ ጀጎ በሰጡት አስተያየት በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ከምንግዜውም በላይ የህዝቧን ድጋፍ ትፈልጋለች ብለዋል።

ለዚህም አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ እንደሆኑ ጠቁመው ወጣቱ እንደ ቀድሞ አባቶቹ ለሀገሩ ታሪክ ሰርቶ ትልቅ ስም ማኖር እንዳበት ተናግረዋል።

በጌዴኦ ዞን  ከ6 ሺህ በላይ የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በማህበር ተደራጅተው  ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቻቸውን ለማቃለል እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም