ብሄራዊ የሴቶች ፖሊሲ ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታውን ባገናዘበ መልኩ ሊሻሻል ነው

93

አዲስ አበባ መጋቢት 7/2013 በኢትዮጵያ ያለው ብሄራዊ የሴቶች ፖሊሲ ከዓለም አቀፉ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተመጣጠነና በሴቶች የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ በሚያስችል መልኩ ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።

የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በብሄራዊ የሴቶች ፖሊሲ ላይ የተደረገ የቅድመ ጥናት ውጤት ከክልል ቢሮዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

ጥናቱ ከአንድ አመት በላይ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን በ1985 ዓ.ም በወጣው ብሄራዊ የሴቶች ፖሊሲ ላይ ዳሰሳ በማድረግ ምክረሃሳብም ቀርቦበታል።

በጥናቱ በተለያዩ ክልሎች ከ60 ወረዳዎች የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳታፊ መሆናቸውን የጥናቱ መሪ ኪያ ገዛኸኝ ተናግረዋል።

በመሆኑም ግኝቱ በመንግስት ተቋማት በፋይናንስና በሰው ኃይል እንዲሁም በቴክኒክ በኩል ያሉ የአቅም ማነስ ክፍተቶች እንዳሉ አመላክቷል ብለዋል።

ውይይቱ የጥናቱን ውጤቶች ለማረጋገጥና ከሚመለከታቸው አካላት ግብአት ለማካተት የሚያስችል መሆኑን የጥናቱ መሪ አብራርተዋል።

ብሄራዊ የሴቶች ፖሊሲ በሴቶች የሚነሱ የተጠቃሚነት ጥያቄዎችን ምላሽ የሚሰጥ እንደሆነም አስረድተዋል።

የፖሊሲው መሻሻል አሁን ካለንበት አገራዊ፣ አህጉራዊና አለምአቀፋዊ ሁኔታና ካለው የሴቶች ፍላጎትና ጥያቄ አኳያ ወሳኝ መሆኑን ያብራሩት ደግሞ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አሀመድ ናቸው።

አገሪቱ ከፖሊሲው በኋላ የተቀበለቻቸው የተለያዩ አለምአቀፍ ድንጋጌዎችና የልማት እቅዶች ጋር የተዋሀደና ጊዜውን የዋጀ ፖሊሲ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

ፖሊሲውን ለመከለስ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የዳሰሳ ጥናት መደረጉን አንስተው የዛሬው መድረክም በግኝቱ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር የተደረገበት ነው ብለዋል።

ቀጣይ መሰል ውይይቶች እንደሚቀጥሉና የቅድመ ጥናቱ ስራ መጠናቀቅን ተከትሎ ወደ ፖሊሲ ክለሳ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የሴቶች መብት እንዲጠበቅና ተሳታፊነትና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀው አሁንም በዚህ ረገድ የሚቀሩ ስራዎችን ለማከናወን የፖሊሲው መከለስ ትልቅ አቅም ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም