የጉበት በሽታን ለመከላከል የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማጎልበት ይገባል-የዓለም የጤና ድርጅት

84
አዲስ አበባ ሐምሌ 21/2010 በአፍሪካ የጉበት በሽታን ለመከላከል ባለድርሻ አካላት በበሽታው ዙሪያ ኅብረተሰቡን ግንዛቤ እንዲያስጨብጡ የዓለም የጤና ድርጅት አሳሰበ። የዓለም የጉበት በሽታ ቀን "የጉበት በሽታን እንመርመር፤ እንከባከብ" በሚል መሪ ሃሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዛሬ እየተከበረ ነው። ለሰውነት መመረዝና ለከባድ ኢንፌክሽን በማጋለጥ ለህልፈተ-ህይወት በሚዳርገው የጉበት በሽታ 'ቢ' እና 'ሲ' በሽታ በአሁኑ ወቀት በዓለም ላይ 323 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የተጠቁ መሆናቸውን የዓለም የጤና ድርጅት ይገልጻል። 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በዚሁ በሽታ በየዓመቱ ለሞት ይጋለጣሉ፤ ይህም ኤችአይቪ/ኤድስ ከሚያስከትለው ጉዳት በአስር እጥፍ ይልቃል ነው የተባለው። በአፍሪካም አሁን ላይ 70 ሚሊዮን ዜጎች በበሽታው ተጠቅተዋል፤ ከእነዚህም ከ10 ሰዎች 9ኙ ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ምርመራ አለማድረጋቸውን መረጃው አመላክቷል። የዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ማትሺዲሶ ሞይቲ እንዳሉት የአፍሪካ አገሮች ይህንን በሽታ ለመከላከል የሚያስችል ጠንካራ ብሔራዊ የጤና ስትራቴጂ ሊዘረጉ ይገባል። በተለይም ቅድመ ምርመራን ለማስፋትና በበሽታውም ከተጠቁ አስፈላጊውን እንክብካቤ ለማድረግ በጤና ሴክተሩ ላይ ከፍተኛ መዋዕለ-ነዋይ ማፍሰስ እንደሚገባም አሳስበዋል። መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በሽታውን ከአህጉሩ ለመከላከል የሚደረገውን መንግሥታዊ ጥረት እንዲያግዙና በተለይም ስለበሽታው ግንዛቤ በመፍጠር እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል። ድርጅታቸውም ለአፍሪካ አገሮች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም