መንግስት የአርሶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ እየሰራ ይገኛል ... ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

89

መጋቢት 4/2013(ኢዜአ) መንግስት የአርሶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ እየሰራ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዛሬው ዕለት በምዕራብ አርሲ ዞን ኤበን አርሲ ወረዳ ሾባ ቡልቱም ቀበሌ በ1 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ የለማ የስንዴ ክላስተርን ጎብኝተዋል፡፡ 

በጉብኝቱም የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰመስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሣ እና የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተገኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር እንዳሉት እጅ ለእጅ ተያይዝንና አንድ ሆነን ከሰራን ይህቺን አገር ከድህነት የምናወጣበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡

መንግስት የአርሶ አደሩ ህይወት እንዲቀየርና በአካባቢውም አስፈላጊው የመሰረት ልማት እንዲሟላለት በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

አርሶ አደሮች ያላቸውን አቅም፣ ጉልበትና መሬት ተጠቅመው ምርትና ምርታማነትን እንዲያበዙ መንግስት እርዳታ እንደሚያደረግላቸውም ገልጸዋል፡፡

የምዕራብ አርሲ ዞን ኤበን አርሲ ወረዳ አርሶ አደሮችም በበጋ መስኖ ባመረቱት ምርት ለሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮች ምሳሌ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሣ በበኩላቸው ክልሉ አገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን የስንዴ ምርት ለማስቀረት እየሰራ ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመትም በበጋ መስኖ በክልሉ 300 ሺህ አርሶ አደሮችን በኩታ ገጠም አስተራረስ በማሳተፍ እስከ አሁን 160 ሺህ ሄክታር መሬት መልማቱን ገልጸዋል፡፡

እስከ በጀት ዓመቱ ፍጻሜም ተጨማሪ 200 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ለመሸፈን መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

አስተያታቸውን የሰጡ አርሶ አደሮች እንዳሉት መንግስት ባደረገላቸው ድጋፍ ስንዴን ለመጀመሪያ ጊዜ በመስኖ ማልማታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዘሩት የስንዴ ምርትም የልፋታቸውን ዋጋ ለማግኘት መዘጋጀታቸውን አክለዋል፡፡

በወረዳው ከስንዴ በተጨማሪ 4 ሺህ 300 ሄክታር መሬት በሽንኩርት፤ ቲማቲም ፤ ድንች እና በሌሎች ምርቶች ተሸፍኗል።

በአካባቢው ለመጀመሪያ ጊዜ መስኖን በመጠቀም የግብርና ስራው ላይ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች መንግስት የትራክተር፤ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም