የህወሓት ቡድን ተላላኪዎች የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመረበሽ በህገወጥ ተግባራት መሰማራታቸው ተገለጸ

91

መጋቢት 4/2013(ኢዜአ) የህወሓት ቡድን ተላላኪዎች ሀሰተኛ ገንዘቦችን በማሰራጨት ህዝቡን ተጎጂ ለማድረግና ኢኮኖሚውን ለማናጋት እየሰሩ ነው ሲሉ የሰሜን ዕዝ የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ተናገሩ።

ከሰሞኑ የአገር መከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ጸጥታ አካላት ባደረጉት ክትትል በመቀሌ ከተማ ህገ-ወጥ ገንዘብ ሲያትሙ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

የሰሜን ዕዝ የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ካሳ መላኩ እንዳሉት ሕገ-ወጦቹ ከ570 ሺህ ብር በላይ ፎርጅድ ወይም ተመሳስሎ የተሰራ ብር በማተም ወደ ህብረተሰቡ ለማሰራጨት ሲያዘጋጁ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።

በዚሁ ወቅትም በርካታ ገንዝብ ወደ ሁመራ፣ የድንበር አካባቢና ሌሎች ቦታዎች ያሰራጩ በመሆኑ ህብረተሰቡ የገንዘብ ልውውጥ ሲያደርግ ወይም ሲገበያይ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

ግለሰቦቹ ህጋዊ ንግድ ፈቃድን ከላላ በማድረግ ሕገ-ወጥ/ፎርጅድ/ የኢትዮጵያ ብር፤ የኤርትራ ናቅፋ እና የተለያዩ አገራት ገንዘቦችን በማተም ህረተሰቡን የማሳሳትና የአገሪቱን ኢኮኖሚ የማናጋት ስራ ሲሰሩ እንደነበር አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት የሕወሓት ቡድንና ተላላኪዎቹ በለመዱት ሕገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተዋል ሲሉ ኃላፊው አስታውቀዋል።

ግለሰቦቹ ህገ- ወጥ ገንዘቦችን ከማተም በተጨማሪ ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች ማሕተሞች ጋር ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት ብለዋል።

የሁመራና የአካባቢው የቀበሌ መታወቂያና ተመሳስለው የተሰሩ ህገወጥ የመታወቂያ ወረቀቶችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሰዋል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ህገ-ወጥ ገንዘቦቹን በአማራና ትግራይ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎችና በሱዳንና ኤርትራ ድንበር አካባቢዎች ማሰራጨታቸውን ተናግረዋል።

ህገ-ወጥ ገንዘቦቹን ወደ ህብረተሰቡ ለማሰራጨትም ትብብር የሚያደርጉ የተወሰኑ የግል ባንኮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በነዚህ አካላት ላይም የጸጥታ አካላት ክትትል እያደረጉ መሆኑን ኮሎኔል ካሳ መላኩ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም