ወጣቱ የአገሩን ሉዓላዊነት ከጠላት በመጠበቅ የዜጎችን በሰላም የመኖር ዋስትና ማረጋገጥ አለበት - ሜጀር ጄኔራል ጌታቸው ገዳሙ

70

መጋቢት 4/2013 ዓም (ኢዜአ) ወጣቱ የአገሩን ሉዓላዊነት ከጠላት በመጠበቅ የዜጎችን በሰላም የመኖር ዋስትና የማረጋገጥ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ከፍተኛ መኮንን ተናገሩ።

ኢትዮጵያ ከውስጥም ሆነ ከውጭ በሚደርስባት ተጽዕኖ ሉዓላዊ የድንበር ግዛቷን ለማስከበር ወጣቶች ብሄራዊ አገልግሎት ሊሰጡ ይገባል ተብሏል።

ኢትዮጵያዊያን የአገራቸውን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር በደምና በአጥንታቸው አስከብረው ለዘመናት በነፃነት መኖርን ባህላቸው ያደረጉ ሕዝቦች ናቸው።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ከፍተኛ መኮንን ሜጀር ጄኔራል ጌታቸው ገዳሙ ለኢዜአ እንዳሉት ወታደርነት ለአገር የጉልበትና የደም መስዋዕትነትን የዓላማ መተሳሰርና ኢትዮጵያዊ አርበኝነትን ይጠይቃል።

በሥነ ምግባር የተኮተኮተ በአዕምሮው የበሰለ አምራች ዜጋ የሚፈጠርበት ሕዝባዊ አደራን መወጣት የሚችል ህዝባዊ መሰረት ያለው የአገርን ዳር ድንበር አስከባሪ ዘብ ነው ይሉታል ወታደርነትን።

በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግስት አድዋ ላይ ዘመናዊ መሳሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን ነጩን የኢጣልያ ሰራዊት በጦርና በጎራዴ አዋርደው የላኩት፤ ከ43 ዓመታት በፊት እብሪተኛውን የሶማሊያ አምባገነናዊ መሪ ዚያድ ባሬ ካራ ማራ ላይ የሽንፈት ጽዋ ያስጎነጩት ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ካላቸው ጥልቅ ፍቅርና አንድነት የመነጨ መሆኑንም ይገልጻሉ።

በመሆኑም የአሁኑ ትውልድ በፖለቲከኖችና ብሄርተኖች የተሳሳተ ትርክት ሳይደናገር፤ የኢትዮጵያ ትክክለኛ ታሪክ በመገንዘብ አባቶቹ በደምና በአጥነታቸው ያቆዩለትን አገር ግንባር ቀደም ሆኖ የመጠበቅ ኃላፊነቱን መወጠጣት አለበት ብለዋል ጄኔራል መኮንኑ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ ምክትል ሊቀ መንበር ዶክተር ጫኔ ከበደና በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ እንዳለ ንጉሴ ወታደራዊ ኃላፊነትን ጨምሮ በተለያዩ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ መስራት የአገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ትልቁና አስፈላጊው ሙያ መሆኑን ይናገራሉ።

ከኢትዮጵያ ያነሰ ታሪክ ያላት አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን አገሮች ዜጎቻቸው ወደ ሌላ ስራ ከመሰማራታቸው በፊት በቅድሚያ የውትድርና/ብሄራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ያደርጋሉ ብለዋል።

በኢትዮጵያም ከ12ኛ ክፍል ጀምሮ በቴክኒክና ሙያ፣ በምህንድስና በሌሎች ሙያዎች የሰለጠኑት ወጣቶች ዘመናዊውን የውትድርና ስልት በመቀላቀል አገራዊ ግዴታቸውና ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ይላሉ።

መከላከያ ሰራዊቱ እውቀትና ክህሎት ባላቸው ወጣቶች መገንባት እንዳለበት የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ከኢትዮጵያ በላይ ትልቅ ነገር አለመኖሩን በመገንዘብ ከቡድንተኝነት አስተሳሰብ መውጣት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ከውጭ ወራሪ ራሷን በመከላከል ሉዓላዊነቷን አስከብራ የኖረችው ጠላቶች ስለሌሏት ሳይሆን፣ ለአገራቸው ደማቸውን የሚገብሩ ጀግኖች ልጆች ስላሏት መሆኑን አስታውሰዋል።

ሜጀር ጄኔራል ጌታቸው ኢትዮጵያ ከቅርቡም ከሩቁም ችግር ባጋጠማት ጊዜ ለመውጋት የሚታትሩ የውጭ ጠላቶች ዛሬም ውስጣዊ ችግራችንን አይተው ሊያጠቁን እየሞከሩ ነው ብለዋል።

አምባገነኑ የሶማሊያ መሪ ዚያድ ባሬ ኢትዮጵያን በ1969 በወረረበት ወቅት ሱዳን በሌላ በኩል ኢትዮጵያን መውጋቷን ለአብነት በመጥቀስ ዛሬም የውስጥ ችግራችንን አይታ ወራናለች ብለዋል።

ወጣቶች ከጥንት ጀምሮ ለኢትዮጵያ የማያንቀላፉ ጠላቶች እንዳሏት በመገንዘብ በሥነ ምግባርና በእውቀት ታንጸው አገራቸውን ከጠላት የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ የአገር መከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ በርካታ ወጣቶች እንዲቀላቀሏቸው እንደሚፈልጉ መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም