በሀላደጌ አሰቦት ዕጩ ብሔራዊ ፓርክ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው

92

ሠመራ፤ መጋቢት 03/2013(ኢዜአ)፡- በአፋርና ኦሮሚያ አጎራባች አካባቢዎች በሚገኘው የሀላደጌ አሰቦት ዕጩ ብሔራዊ ፓርክ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አስታወቁ።

አሚባራ የሚገኘው የጽህፈት ቤቱ አስተባባሪ  አቶ አህመድ እድሪስ ለኢዜአ እንደተናገሩት ፤ የእሳት ቃጠሎው የተነሳው ከትናንት እኩለ ቀን ጀምሮ በፓርኩ ሰሜናዊ ክፍል ሰው ሰራሽ በሆነ ችግር እንደሆነ ይገመታል።

ቃጠሎውን ለመቆጣጠር በአካባቢው ከሚገኙ የአሚበራና ሃሩካ ወረዳዎች አመራሮች እንዲሁም የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የልማት ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአካባቢው ከሚነፍሳው ከባድ ነፋስና ሙቀት ጋር ተዳምሮ እሳቱን የመቆጣጠር ስራው ፈታኝ አድርጎታል ብለዋል።

ቃጠሎው ስፋት ባለው   የፓርኩ እጽዋት ፣ ሰጎን እና ሌሎችም የዱር እንስሳት ላይ ጉዳት እንዳደረሰ ይገመታል ያሉት አስተባባሪው ጠቁመው አሁን ላይ እሳቱ እየጠፋና እየቀነሰ በመሆኑ መቆጣጠር የሚቻልበት እድል መኖሩን ተናግረዋል።

መንስኤውና የደረሰው ጉዳቱ መጠን በቀጣይ  ተለይቶ ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የሃላይደጌ አሰቦት ዕጩ ብሔራዊ ፓርክ በ1965 ዓ.ም. የተመሠረተ ሲሆን በውስጡም የሜዳ አህያ፣ ሳላ ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሜዳ ፍየልን ጨምሮ የተለያዩ አእዋፍና እጽዋት ዝርያዎች የሚገኝበት መሆኑንን ከአስተባባሪው ገለጻ ለመረዳት ተችላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም