የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳቸው ከሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሴቶች ዋነኞቹ ናቸው - ዶክተር ሊያ ታደሰ

65

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2/2013 ( ኢዜአ)  የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳቸው ከሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሴቶች ዋነኞቹ መሆናቸውን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለፁ፡፡
የጤና ሚኒስቴር ሠራተኞች ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን አክብረዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ባስተላለፉት መልዕክት ሴቶች ከቤተሰብ ጀምሮ በእያንዳንዱ ዘርፍ የማኅበረሰብ ጤናን በመገንባት ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ይሁንና በዓለምና በኢትዮጵያም የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳቸው ከሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዋነኞቹ ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም ገቢያቸው አነስተኛ የሆኑ ሴቶች ቫይረሱ ከሚያሳድርባቸው ማኅበራዊና አካላዊ ጫና በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

መንግስት ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ለችግር ለተጋለጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኅብረተሰቡም ለተቸገሩ ሴቶች፣ ለአቅመ ደካሞች፣ ለአረጋዊያንና ለአካል ጉዳተኛ ሴቶች ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዶክተር ሊያ ሴቶች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጽዕኖዎችን ተቋቁመው በመውጣት ያልተገደበ መብታቸውን እንዲያጣጥሙ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት መስራት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ በጤናው ዘርፍ ከሚከናወኑ ተግባራት አንዱና ዋነኛው የሴቶችና የእናቶች ጤና አጠባበቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሴቶች ባሉባቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኃላፊነቶች ሳቢያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የታመሙትን በመንከባከብ ሂደት ለቫይረሱ ተጋላጭነታቸው ከፍያለ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

ለዚህም የኮቪድ-19 ቫይረስ ከተገኘባቸው መካከል 39 በመቶዎቹ፤ በቫይረሱ ሕይወታቸው ካለፈ ዜጎች መካከል ደግሞ 37 በመቶ ያህሉ ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን አስመልክተው የተናገሩት የሚኒስቴሩ የህጻናትና ወጣቶች ዳይሬክተር ወይዘሮ ፋጡማ ሰዒድ ደግሞ ሴቶች በአገር ሠላምና ግንባታ ያላቸውን ጉልህ ድርሻ አውስተዋል።

በዓለም ዙሪያ ያለው ፍላጎት ቀጣይነት ያለው በመሆኑ በየትኛውም ስፍራ የሚኖር ግለሰብ ለሴቶች እኩልነትና አዎንታዊ ድሎች መታገል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ሠራተኞች ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን "የሴቶችን መብት የሚያከብር ማኅበረሰብ እንገንባ" በሚል መሪ ሃሳብ አክብረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም