ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የነበረን ቆይታ ለቀጣይ ሥራችን መነሳሳት ፍጥሯል...የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ መምህራን

73
ሚዛን ሀምሌ 20/2010 ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ ጋር የነበረን ቆይታ ለቀጣይ ሥራችን መነሳሳት ፈጥሮልናል ሲሉ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ገለጹ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በአገሪቱ ከሚገኙ 50 ዩኒቨርሲቲዎች ከተውጣጡ ከ3 ሺህ በላይ ምሁራን ጋር በትምህርትና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በቅርቡ መወያየታቸው የሚታወስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያደረጉት ውይይት በቀጣይ ሥራቸውን በተሻለ ለማከናወን መነሳሳት ፈጥሮላቸዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ክፍል መምህር ታደሰ አይበራ እንዳሉት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የነበራቸው ቆይታ ከተለመደው የውይይት አካሄድ የተለየ፣ ሀሳብ በነጻነት የተንሸራሸረበትና በቀላሉ መግባባት የተቻለበት ነው፡፡ ከመድረኩ ተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርበው እንደነበር አስታውሰው አብዛኞቹ በትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት ያደረጉ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ "በውይይቱ ላይ የትምህርት ጥራት ለአገር ዕድገት መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ብቁ የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት እንዳለባቸው የጋራ ግንዛቤ ይዘናል" ብለዋል፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የምርምርና የልህቀት ማዕከል ማድረግ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ በመሆኑ ተቋማቱን ብቃት ባለው የሰው ኃይልና በግብዓት በማሟላት የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ የበኩላቸውን ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በውይይቱ የትምህርት ተቋማት ከፖለቲካ ነጻ ሆነው ተልኳቸውን መፈጸም እንዳለባቸው ግንዛቤ መያዛቸውን የገለጹት መምህር ታደሰ፣  "በቀጣይ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ነጻ የትምህርት ሂደት እንዲኖር ትኩረት ሰጥቼ እሰራለሁ " ብለዋል፡፡ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተርና መምህር ታገል ወንድሙ በበኩላቸው " መድረኩ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ሁላችንም የድርሻችንን ለመወጣት የቤት ሥራ የወሰድንበት ነው" ብለዋል፡፡ የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተቋቋሙበት አካባቢ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን መደገፍ እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት በቀጣይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል። በትምህርት ዘርፍ የሚስተዋሉ መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታት በውይይት መድረኩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ያስቀመጡትን አቅጣጫዎች በተቋማቸው ወደተግባር እንዲቀየር አበክረው እንደሚሰሩም አመልክተዋል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያደረጉት ውይይት ከትምህርት ሥርዓቱ ባለፈ በተለያዩ አገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጭምር ያተኮረ እንደነበር የገለጹት ደግሞ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን ካሳ ናቸው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተመዘገበውን ሁለንተናዊ ለውጥ ማስቀጠል በሚቻልበትና የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ምን ሊሆን እንደሚገባ በተደረገ ውይይት ሰፊ ግንዛቤ መያዛቸውን ገልጸዋል። የትምህርት ጥራት እንዲሻሻልና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚታዩ ችግሮች እንዲፈቱ መንግስት ያዘጋጀውን አዲሱን የትምህርት ሥርዓት ፈጥኖ መተግበር እንዳለበት ጠቁመው፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የነበራቸው ቆይታ ለቀጣይ ሥራቸው ተስፋ የሰነቁበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም