ዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊ የሥራ ፈጠራ ፖሊሲ ማስተግበሪያ መመሪያ አዘጋጀ

74

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2013 /ኢዜአ/ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን የማኅበራዊ የሥራ ፈጠራ ፖሊሲ ማስተግበሪያ መመሪያ አዘጋጅቶ ማጠናቀቁን ገለጸ።

ዩኒቨርሲቲው በኢትዮጵያ የማኅበራዊ የሥራ ፈጠራ ሚና፣ ተግዳሮትና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።  

የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ምትኬ ሞላ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፣ ተቋሙ ማኅበራዊ የሥራ ፈጠራ ምህዳር እንዲስፋፋ እየሰራ ነው።

ከኢንዱስትሪዎችና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር የፖሊሲ ሠነድ ዝግጅትን ጨምሮ በርካታ ሙያዊ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሥራ ፈጠራ ሀሳቦችን ወደ ተግባር መቀየር የሚያስችሉ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ነው የገለጹት።

ይህንን ተከትሎም ዩኒቨርሲቲው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን የማኅበራዊ የሥራ ፈጠራ ፖሊሲ ማስተግበሪያ መመሪያ አዘጋጅቶ ማጠናቀቁን ጠቁመዋል።

መመሪያው ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰራበት መቆየቱን ገልጸው የመጨረሻ ማሻሻያና አስተያየት ተደርጎበት እንደተጠናቀቀ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት መመሪያውን ለማውጣት የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።  

"መመሪያው ወደ ሥራ ሲገባ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የሥራ ፈጠራ ሃሳባቸውን በምን መልኩ ወደ ተግባር  መቀየር እንደሚችሉ ሁኔታዎችን ያመቻቻል" ብለዋል።

በተለይም ደግሞ ማኅበረሰቡና ዩኒቨርሲቲው በነዚህ የፈጠራ ሥራዎች መቆራኘት እንዳለባቸው አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ጠቁመዋል።

"ዩኒቨርሲቲው ከኢንዱስትሪ ጋር ያለውን ግንኙነት በተደራጀ አኳኋን መልክ ለማስያዝም መመሪያው ትልቅ እገዛ  ያደርጋል" ብለዋል ዶክተር ምትኬ።

የዩኒቨርሲቲው የማኔጅመት መምህር ዶክተር ባንቴ ወርቄ በበኩላቸው "በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ሥራ ፈጠራን በተመለከተ ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፍ የለም" ነው ያሉት።

በመሆኑም የሚመለከተው አካል የሥራ ፈጣሪዎችን በቀላሉ ሊያበረታታና ዘርፉን ሊያሳልጥ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ማውጣት እንዳለበት አመልክተዋል።  

ጎን ለጎንም መንግስት በዘርፉ ለመሰማራት ሃሳብና ፍላጎት ላላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች አስፈላጊውን ድጋፍ መስጠትና ማበረታታት እንደሚገባው ጠቁመዋል።

"ባንኮችም ለነዚህን የዘርፉ ተዋናዮች ልክ እንደ ሌሎቹ አገራት የሥራ ፈጠራ ሃሳቦችን ብቻ መሰረት አድርገው ያለ ማስያዣ ብድር የሚያቀርቡበት ማዕቀፍ መፍጠር አለባቸው" ነው ያሉት።  

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ53 ሺህ በላይ በማኅበራዊ የሥራ ፈጠራ ዘርፍ የተሰማሩ ሥራ ፈጣሪዎች መኖራቸው በመድረኩ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም