የልማት ጀግና በሆኑት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ገለጹ

98
የመቀሌ/ሽሬ/ደብረ ብርሃን/ሀረር ሀምሌ 20/2010 የልማት ጀግና በሆኑት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን የመቀሌ፣ ሽሬ እንዳስላሴ፣ ደብረ ብርሀንና ሐረር ከተሞች ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋሪዎቹ በኢንጂነር ስመኘው ግንባር ቀደም መሪነት ግንባታው ሲከናወን የነበረውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከዳር ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀሱም ገልጸዋል። አስተያታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ የግድቡ ግንባታ ከግብ እንዲደርስ የጎላ አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ የነበሩ ታላቅ ሰው ናቸው። የአገሪቱ ገጽታ እንዲቀየርና የታችኛው ተፋሰስ አገራት በአባይ ወንዝ ላይ የጋራ ተጠቃሚነትን በሚገባ እንዲገነዘቡ በተደረጉ ጥረቶች ሁሉ ኢንጂነሩ የጎላ ሚና እንደነበራቸው አስታውሰዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ውጤት የሆነውን የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ የማየት እድል ባያጋጥማቸውም ህዝቡ በግድቡ ላይ ተሳትፎው እንዲጎለብት ያደረጉ የልማት ጀግና ሆነው ማለፋቸው ሁሌም እንዲታወሱ የሚያደርጋቸው መሆኑን ነው የገለጹት በኢጅነር ስመኘው ድንገተኛ ሞት ጥልቅ ሃዘን ቢሰማቸውም በኢንጂነሩ ግንባር ቀደምነት እየተከናወነ ያለውን የሕዳሴ ግድብ ከዳር ለማድረስ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉም ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል። የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው ኢንጂነር ስመኘው በቀለ የልማት ጀግናና ዘመን የማይሽረው ታሪክ የሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። በኢንጂነሩ ሞት የከፋ ሀዘን ቢሰማቸውም የእርሳቸው ህልፈት የጀመሩትን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዳር ከማድረስ እንደማያግዳቸው ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ ኢንጂነር ስመኘው በሕይወት ዘመናቸው ለአገርና ለህዝብ ጠቀሜታ ያለው ሥራ ሰርተው ያለፉ የልማት ጀግና መሆናቸውንም መስክረዋል። ዛሬ በህይውት ባይኖሩም መልካም ስራቸው ሁሌም ስማቸውን ህያው እንደሚያደርገው ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን የገለጹት የሕዳሴውን ግድብ ለማጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በማረጋገጥ ነው። ነዋሪዎቹ ኢንጂነር ስመኘው በተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሌት ተቀን ህዝብና አገርን ያገለገሉ መሆናቸውን ገልጸው ህይወታቸው ድንገት በማለፉ ከፍተኛ ሀዘን እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡ ኢንጂነር ስመኘው ሁሌም ስማቸውን ከፍ አድርጎ የሚያስጠራ ሥራ ሲሰሩ መቆየታቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ የህዳሴውን ግድብ ከዳር ለማድረስ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡ በተመሳሳይ ዜና የሀረር ከተማ ነዋሪዎች፣ የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ሠራተኞችና የሀረር ከተማ ማርሽ ባንድ ማህበር በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልፀዋል። ነዋሪዎቹና ሠራተኞቹ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ የታገሉና ሌት ተቀን ሲደክሙ የኖሩ ሰው መሆናቸውን ተናግረዋል። በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው የገለጹት የየከተሞቹ ነዋሪዎች ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ለሰራ ባልደረቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መፅናናትን ተመኝተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም