ለተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በትግራይ የሕግ ማስከበርና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ተሰጠ

69

መጋቢት 1/2013(ኢዜአ) የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከ50 ለሚበልጡ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በክልሉ በተከናወነው የሕግ ማስከበርና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጠ።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ በህወሓት የጥፋት ቡድን የደረሱ ጉዳቶችን ለአምባሳደሮቹ ገለጻ አድርገዋል።

የአገር መከላከያ ሠራዊት የሕግ ማስከበር ተግባሩን በአጭር ጊዜ ማከናወን ባይችል ኖሮ የጥፋት ቡድኑ አገር የማፈራረስ ተልዕኮ እንደነበረውም ተናግረዋል።

በመንግስት በኩል የሕግ ማስከበር ተግባር የተከናወነው የጥፋት ቡድኑ በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባላት ላይ በፈጸመው ጥቃት ምክንያት መሆኑንም ዶክተር ሙሉ ገልፀዋል።

"በአሁኑ ወቅት በክልሉ ሠላም የማስፈንና ሠብዓዊ ድጋፍ የማቅረብ ሥራው በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ነው" ብለዋል።

ዶክተር ሙሉ የጥፋት ቡድኑ በተለያዩ መሰረተ ልማቶች ላይ ያደረሰውን ጉዳት የመጠገንና ዳግም ለአገልግሎት እንዲውሉ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የሠብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ አቶ አግዘው ህዳሩ የጥፋት ቡድኑ በክልሉ በሚገኙ ፋብሪካዎችና መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማደረሱን ገልጸዋል።

በዚህም ከ11 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ሀብትና ንብረቶች መውደማቸውን ነው የተናገሩት።

በፋብሪካዎችና መሰረተ ልማቶች ላይ በደረሰው ጉዳት 52 ሺህ የሚሆኑ የኢፈርት ሠራተኞች መበተናቸውንም ገልፀዋል።

ከ2 ሺህ 500 በላይ ትምህርት ቤቶች በመውደማቸው ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚበልጡ ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል ብለዋል ያሉት።

በገጠር አካባቢ የጥፋት ቡድኑ በርካታ እንስሳት መዝረፉንና መሰል ጉዳቶች መፈጸማቸውንም አመልክተው፤ በእነዚህ ምክንያቶችም በክልሉ  4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች ለችግር መዳረጋቸውን አስረድተዋል።

ከእነዚህ መካከል 1 ሚሊዮን የሚሆኑት ቀደም ሲልም በሴፍቲኔት ሲረዱ የነበሩ ሲሆኑ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮኑ ደግሞ በተፈጠረው ችግር እርዳታ ለመጠበቅ የተዳረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ለእነዚህ ድጋፍ ፈላጊዎች 77 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው፤ ድጋፍ ከሚፈልጉት መካከል 77 በመቶ ለሚሆኑት ሰብዓዊ ድጋፍ የማድረስ ተግባር መከናወኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም