የህወሓት ጁንታ በሰው ልጅ ላይ ሊፈጸም የማይችል ግፍ ፈጽሞብናል - የሰሜን ዕዝ አባላት

58

መጋቢት 1 /2013 (ኢዜአ) "ጽንፈኛው የህውሓት ጁንታ በሰው ልጅ ላይ ሊፈጸም የማይችል ግፍ ፈጽሞብናል" ሲሉ በህክምና ላይ የሚገኙ የሰሜን ዕዝ አባላት ተናገሩ።

ምክትል መቶ አለቃ ዳዊት ደርቤ "በወገን ጥቃት ይደርስብናል ብለን ባለሰብንበት ወቅት በሌሊት በመጥረቢያ እጄ ተቆረጠ" ይላል።

"ሞቷል ብለው ትተውኝ ስለሄዱ ተረፍኩ፤ ሌሎች የሰራዊቱ አባላት ግን በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ" ሲል ይገልጻል።

"ጁንታው በሰራዊቱ ላይ የፈጸመው ግፍ በጽኑ መወገዝ ያለበት ድርጊት ነው" የሚለው ተጎጂው፤ "በወገን ላይ ቀርቶ በጠላት ላይ ሊፈጸም የማይገባ ግፍ ነው" ብሏል።

ሌላው የሰራዊቱ አባል ሻለቃ ባሊና ሰሚ ተመሳሳይ ጥቃት እንደደረሰበት ይናገራል።

"ሰራዊቱ የክልሉን ህዝብ በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሲያግዝ ቆይቶ ቢሆንም ለውለታው የተከፈለው አሰቃቂና አሳዛኝ ግፍ ነው" ብለዋል።

ቡድኑ በሰራዊቱ አባላት ላይ ከፈጸመው በደል በተጨማሪ በሰሜን ዕዝ ውስጥ የሚገኘው የመቀሌ መከላከያ ሶስተኛ ደረጃ ሆስፒታልን ጨምሮ የሰራዊቱ የተለያዩ ንብረቶችን እንዳወደመ ጠቁመዋል።

ሆስፒታሉ ጉዳት ሳይደርስበት በፊት ለሰራዊቱ፣ ለሰራዊቱ ቤተሰቦችና እና ለአካባቢው ነዋሪዎች እስከ ቀዶ ህክምና ድረስ አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ "ጁንታው ሆስፒታሉን ሙሉ በሙሉ በመዝረፍና በማውደም ለህዝብ ያለውን ንቀት በተግባር አሳይቷል" ብለዋል።

በመቀሌ የመከላከያ ሶስተኛ ደረጃ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ሻለቃ ዶክተር ከበደ አደለ የሆስፒታሉ ንብረት ሙሉ በሙሉ በጁንታው መውደሙን አረጋግጠዋል።

"ሆስፒታሉ 160 አልጋዎች ያሉት ሲሆን ከመከላከያ ሰራዊት በተጨማሪ ለዜጎች አገልግሎት እየሰጠ ነበር" ያሉት ሜዲካል ዳይሬክተሩ፤ መንግስት አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማሟላት ሆስፒታሉን ወደ ስራ መመለሱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም