ለመጭው መኽር የሚያገለግል 7 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እየተደረገ ነው-የአማራ ግብርና ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
ለመጭው መኽር የሚያገለግል 7 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እየተደረገ ነው-የአማራ ግብርና ቢሮ
136
ባህር ዳር የካቲት 25/2013 (ኢዜአ ) በአማራ ክልል ለመጭው የመኽር ወቅት ለምርት ማሳደጊያ የሚያገለግል 7 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ አስቀድሞ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የግብርና ግብዓትና የገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ተወካይ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሽራ ሲሳይ ለኢዜአ እንደገለጹት ለ2013/14 ምርት ዘመን መኽር ወቅት ለምርት ማሳደጊያ የሚያገለግል 7 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ የዘር ወቅት ከመድረሱ በፊት ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እየተደረገ ነው።
ለምርት ወቅቱ ከሚያስፈልገው ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታሉ ተጓጉዞ ወደ ክልሉ መግባቱን ተናግረዋል።
ወደ ክልሉ ከገባው ማዳበሪያ ውስጥ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታሉ በህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ለአርሶ አደሩ እየደረሰ መሆኑን ገልፀዋል።
ማዳበሪያው የክረምት ወቅቱ ከመግባቱ በፊት የመንገድ አማራጭ በሌለባቸው አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎችና ቀድመው ሰብል በሚያለሙ አካባቢዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራጨ መሆኑን አመልክተዋል።
ቀሪውን ማዳበሪያ እስከ ሰኔ 15 ቀን 2013 ዓም ሙሉ በሙሉ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ገብቶ ጥቅም ላይ መዋሉን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።