ሰላም እንዳይናጋና አገራዊ ለውጡ እንዳይደናቀፍ ህዝቡ ሰላሙን ነቅቶ ሊጠብቅ ይገባል-አቶ ሚሊዮን ማቲያስ

60
ሀዋሳ ሀምሌ 20/2010 በደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ችግሮች የህዝቡን ሰላማዊ ኑሮ እንዳያናጉና በአገሪቱ የተጀመሩ ለውጦችን እንዳያደናቅፉ መላው የክልሉ ህዝብ ሰላሙን ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሳሰቡ፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሚሊዮን ማቲያስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ህዝቡ ያለውን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድና በህገመንግስቱ መሰረት ማቅረብ አለበት፡፡ ከዞንና ከወረዳ መዋቅር ጋር በተያያዘ በተለያዩ አካባቢዎች የህዝብ ጥያቄዎች እየቀረቡ እንደሚገኝ ጠቁመው መንግስትና የክልሉ መሪ ፓርቲ ደኢህዴን ለህዝብ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ጥናት በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ በጋሞጎፋ ዞን የቀረበውን የህዝብ ጥያቄ የክልሉ መንግስት እየገመገመ ባለበት በአሁኑ ወቅት ትናንት በሳውላ ከተማ በተነሳ ሁከትና ግርግር በርካታ የመንግስት ተቋማት መውደማቸው አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ህዝቡ ያለውን ጥያቄ ወደብጥብጥ እንዲቀየር ለማድረግና በህዝቦች መካከል ያለውን አብሮነት ለማጥፋት የሚፈልጉ ኃይሎች መጠቀሚያ መሆን እንደሌለበትም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል፡፡ በጋሞ ጎፋ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም ጭምር ተመሳሳይ የመዋቅር ጥያቄዎች እንደሚቀርቡ አቶ ሚሊዮን ገልጸው፣ ከመዋቅር አንጻር እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ በአሁኑ ውቅት የክልሉ የጸጥታ ኃይል ግጭቶችና ሁከቶች በተፈጠሩባቸው አካባቢዎች ሰላምን የማስከበር ሥራ እየሰራ በመሆኑ ህዝቡ የጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል፡፡ በአመራር ድክመት በአግባቡ ያልተመለሱ ቅሬታዎችን ህዝቡ በአንድ ጀንበር መመለስ እንደማይቻል ተረድቶ እስካሁን የተከናወኑ ልማቶችን ከጉዳት መከላከል እንዳለበትም አቶ ሚሊዮን አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም በቅርቡ የጸደቀውን የምህረት አዋጅ ተከትሎ በክልሉ ይርጋለምና አርባ ምንጭ ከተማ በሚገኙ ማረሚያ ተቋማት የተፈጠረው ሁከት ተገቢ አለመሆኑን የገለጹት አቶ ሚሊዮን " ታራሚዎች በምህረት አዋጁ መሰረት በተገቢው መንገድ እንደሚስተናገዱ ማወቅ ይኖርባቸዋል" ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለይ በከተሞች ህገወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ እየተፈጸመ መሆኑን ጠቁመው ይህ ተግባር ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ በነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም