“የመጣነው ሥራ ልናስጀምር እንጂ ድንጋይ ለማስቀመጥ አይደለም”- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

541

የካቲት 28/2013(ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአማራ ክልል የዱርቤቴ -ቁንዝላ-ሻኁራ-ፍንጅት ምዕራፍ አንድ እና ገላጎ-ገንደውሃ ምዕራፍ ሦስት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን አስጀምረዋል።

በወቅቱም “እኛ የመጣነው ሥራ ልናስጀምር እንጂ ድንጋይ ለማስቀመጥ አይደለም” በማለት ስራው ፈጥኖ እንዲጀመር በአጽንኦት ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በአማራ ክልል ዱርቤቴ ከተማ የዱርቤቴ-ቁንዝላ-ገላጎ-መተማ መንገድ ግንባታ አካል የሆነውን የዱርቤቴ -ቁንዝላ-ሻኁራ-ፍንጅት ምዕራፍ አንድ እና ገላጎ-ገንደውሃ ምዕራፍ ሦስት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ባስጀመሩበት ወቅት ነው፡፡

በግንባታ ማስጀመር ሥነስርዓቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ ተገኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት በመርሃግብሩ ላይ ለተገኘው የአካባቢው ማህበረሰብ “የመንገድ ጥናት ከጨረስን በኋላ፣ ጨረታ ካወጣንና የሚሠራውን ተቋራጭ ካወቅን፤ ሥራ ልናስጀምር እንጂ ድንጋይ ልናስቀምጥ አይደለም የመጣነው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

“እኛ የማንጨርሰውን አንጀምርም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ሁሉም በባለቤትነት በመሥራት ቢያግዝ ተመልሰን ሪቫን እንቆርጣለን” ብለዋል፡፡

ግንባታው መንገዱ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ያሉ ምርቶች ከጎንደር-መተማ ከሚሄዱ ይልቅ ከዱርቤቴ-መተማ እንዲሄዱ ዕድል ይሠጣል፤ ከመሀል አገር ጋርም ያገናኛል ብለዋል።

ግንባታው ሲጠናቀቅም በአካባቢው ኢንቨስትመንትና መሠረተ ልማቶች እንዲፋፉ በማስቻል የልማት ትልሞች እንዲሳኩ ያግዛል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

“ለእኛም መጀመር ብቻ ሳይሆን መጨረስ እንደምንችል ለህዝባችን የምናሳይበት የጋራ ማህተማችን ነው” በማለትም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው ፕሮጀክቶችን በሚጠበቀው የጥራት ደረጃ ከተሰጠው የግንባታ ጊዜ ቀድሞ በመጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን ለማስቻል ሁሉም ድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

ለመንገዱ ግንባታ ስኬት ባለስልጣኑ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግምና ህብረተሠቡም ይህንን ወሣኝ ፕሮጀክት በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ተገቢውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግ አደራ ብለዋል፡፡

የአካባቢው ማህበረሰብም መንግስት የህዝቡን ጥያቄ አድምጦ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት የተጀመረ ፕሮጀክት በመሆኑ ተጠናቆ አገልግሎት ይሰጥ ዘንድ ህብረተሰቡ ከባለስልጣኑና ከሥራ ተቋራጩ፣ ከአማካሪ ድርጅት ጎን በመቆም ለፕሮጀክቱ ስኬት የበኩሉን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

አጠቃላይ የግንባታ ወጪው የሚሸፈነው በኢትዮጵያ መንግስት ሲሆን ለማጠናቀቅ 3 ዓመት ከ6 ወራት ዕቅድ ይወስዳል።

የመንገድ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ሥራ የሚያካሂደው ዚጂያንግ ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ግሩፕ የተባለ ዓለም አቀፍ የቻይና ሥራ ተቋራጭ ነው፡፡

በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ ለሚገነቡት ፕሮጀክቶቹ በ5 ቢሊዮን 374 ሚሊዮን 304 ሺህ 301 ብር በጀት ተይዞለታል፡፡

የፕሮጀክቱን ጥራት የሚቆጣጠርና አማካሪ በጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

መነሻው ደቡብ አቸፈር ወረዳ ዱርቤቴ ከተማ ምዕራፍ አንድ 135 ነጥብ 5 ኪ.ሜ የሚረዝመው በዱርቤቴ-ቁንዝላ-ሻኁራ-ፍንጅት የሚያልፍ ነው፡፡

በገላጎ-ገንደውሃ የሚያልፈው ምዕራፍ ሦስት ደግሞ 125 ነጥብ 5 ኪ.ሜ ርዝማኔ ያለው መንገድ ፕሮጀክት ነው ተብሏል፡፡

በዛሬው ዕለት የተጀመሩት ሁለቱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶቹ በጠጠር ደረጃ ያሉና በአገልግሎት ብዛት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው፡፡