በመደመር እሳቤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ወደ ብልፅግና ልናሻግር ይገባል- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

69

የካቲት 28/2013 (ኢዜአ)- ''ዛሬም እንደ ትናንቱ በመደመር እሳቤ ህዝቦች እርስ በእርስ በመተባበር ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊነትን ወደ ብልፅግና ልናሻግር ይገባል'' ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስገነዘቡ።

ከዱር ቤቴ ገንዳ ውሃ የሚገነቡ 260 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው የሁለት የአስፓልት ኮንክሪት መንገዶች ግንባታ ዛሬ ተጀምሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስነ ስርአቱ ላይ እንዳሉት ለዛሬ ወጣቶች አደራ የምለው ኢትዮጵያን እንዲጠብቁ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለእኛ ብርቅ ሃገር እንደመሆኗ ሁሉ ባንጻሩ ብዙ የሚቀኑባትና ብዙ ደግሞ የሚጠሏት፣ ስሟን ሊቀይሩ የሚፈልጉ መኖራቸውን በመግለጽ "ላለፉት ሺህ ዓመታት አልተቻላቸውም "ብለዋል።

"የአሁኑ ትውልድ ከአባቶቻችን የተቀበልናትን ብርቅ ሃገር ጠብቀን ፣ አሳምረንና አስውበን ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ አለብን" ሲሉ ተናግረዋል።

ዛሬም ላይ በመደመር እሳቤ ህዝቦች በመተባበር ኢትዮጵያና ኢትዮጰያነትን በመጠበቅና በማሳደግ ወደ ብልፅግና ለማሸጋገር የሚደረገውን ጎዞ ማሳካት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

"ጎጃም ከሌሎች ህዝቦች ጋር ተዋዶና ተግባብቶ መኖርን ያውቅበታል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝቡ የመደመርን እሳቤ በተግባር ኖሮ ያሳየ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የለውጥ አመራሩ የህዝቡን የልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመመለስ አበክሮ እየሰራ መሆኑን አመልክተው" የማይጨረሱ ስራዎች አይጀመሩም፤ የተጀመሩ ደግሞ ሳይጨረሱ አይቀሩም'' ብለዋል።

የሚገነቡት መንገዶች የአካባቢውን ልማት ለማፋጠን ከማገዙም በላይ በአካባቢው የሚመረቱ የሰብል ምርቶችን ወደ መሃል ሀገር ለማቅረብ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አመላክተዋል።

የመንገድ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ የአካባቢው ማህበረሰብ ተገቢውን እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

"የለውጥ አመራሩ ላለፉት ዓመታት በክልሉ ይስተዋል የነበረውን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ችግር እየፈታ ነው" ያሉት ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር ናቸው።

"ቀደም ሲል በግልፅ ይስተዋል የነበረው ከሃገሪቱ ሃብት የፍትሃዊ ተጠቀሚነት ችግር እንዲፈታ በተደረገው ጠንካራ ትግል ይህ ለውጥ መጥቷል" ብለዋል።

በተገኘው ለውጥ የአማራ ክልል ህዝብ የረዥም አመታት ጥያቄዎቹ እንዲፈቱ ሰፊ እድል መፍጠሩን አመልክተው ግንባታቸው የተጀመሩ መንገዶችተጨባጭ ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይም በመንገድ ዘርፍ እየተሰጡ ላሉ ምላሾች የክልሉ መንግስት አድናቆት እንዳለው ጠቁመው በቀጣይ ቀሪ የልማት ጥያቄዎች እንዲፈቱ ጥረቱ የሚቀጥል መሆኑን አመላክተዋል።

የዱር ቤት ገንዳ ውሃ ያለው የ260 ኪሎ ሜትር መንገዶች አካባቢውን በልማት ከማስተሳሰር ባለፈ ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት የላቀ ድርሻ እንዳላቸው አመልክተዋል።

"ግንባታው የተጀመረው መንገዶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለተፈለገው አላማ እንዲውሉና ባለሃብቱም ሆነ አርሶ አደሩ ምርቱን ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ተጠቀሚ እንዲሆን ተገቢው ክትትል ይደረጋል" ሲሉ አቶ አገኘሁ አስታውቀዋል።

የኢትዮጰያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ተገኝ በበኩላቸው ከለውጡ ወዲህ በሃገሪቱ ታላላቅ የመንገድ መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል።

ሃገሪቱን የመስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከሆኑ ከሱማሌ፣ ከኬኒያ፣ ከጂቡቲ፣ ከኤርትራ፣ ጋር የሚያስተሳሰሩ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።

ከዱር ቤቴ ገንዳ ውሃ የተጀመሩት 260 ኪሎ ሜትር መንገዶች 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በኢትዮጰያ መንግስት ወጭ የሚደረግባቸው መሆኑን ገልፀዋል።

መንገዶቹ ከ4ሺህ ለሚበልጡ ወገኖች የስራ እድል መፍጠር እንደሚችሉ አብራርተዋል።

መንገዶቹ በሦስት አመት ተኩል የሚጠናቀቁ ሲሆን ለአገልግሎት ሲበቁ በአካባቢው በስፋት የሚመረተውን ጤፍ፣ በቆሎ፣ አኩሪ አተርና ሌሎች ሰብሎች ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እንደሚያግዙ አመልክተዋል።

መንገዶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ማድረግ የግድ መሆኑን አመልክተው ለተግባራዊነቱ የአካባቢው ህዝብ ወሰን በማስከበርና ሰላምን በማስጠበቅ ብርቱ ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በመንገድ ግንባታ ማስጀመሪያ ስነ ስርአቱ ላይ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገርና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።እንዲሁም በቆጋ መስኖ ፕሮጀክት የለማ የስንዴ ምርት ተጎብኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም