የጎርጎራ ፕሮጀክት የአካባቢውን ታሪክና ቅርስ ተፈጥሮአዊ ይዘቱን በጠበቀ መንገድ ለቱሪዝም መዳረሻነት ለማዋል ያለመ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትሩ

94

ጎንደር የካቲት 28/2013 (ኢዜአ ) የጎርጎራ ፕሮጀክት ለዘመናት የተሻገረውን የአካባቢውን ታሪክና ቅርስ ተፈጥሮአዊ ይዘቱን በጠበቀ መንገድ ለቱሪዝም መዳረሻነት ለማዋል አላማ ያደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ አስታወቁ።

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ  የገበታ ለሀገር ጎርጎራ ፕሮጀክት ግንባታ መሰረተ ድንጋይ በማስቀመጥ በይፋ አስጀምረዋል።

 የጎርጎራ ፕሮጀክት ግንባታ ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት የጎርጎራ ህዝብ ላለፉት 700 ዓመታት የአካባቢውን ታሪክና ቅርስ ጠብቆ ያቆየ ታላቅ ህዝብ ነው።

 ጎርጎራ በእጅ የያዙት ወርቅ እንደሚባለው ለዘመናት ጥቅም ሳይሰጥ ድብቅ ሆኖ የቆየ ታሪካዊ ስፍራ እንደሆነም አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱ አካባቢውን ወደ ብልጽግና ማማ መዳረሻ ለማሻገር የሚደረገው ጥረት ማሳያ በመሆኑ ህብረተሰቡ

ለፕሮጀክቱ መሳካት አበክሮ እንዲሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው "ጎርጎራና አካባቢው የልማቱ ተቋዳሽና ተጠቃሚ ሳይሆን ለበርካታ አመታት ተጎድቶ የቆየ ነው" ብለዋል።

 የጎርጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የህዝቡን የዘመናት የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የተነደፈ ሀገራዊና ክልላዊ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።

 "ለፕሮጀክቱ ፍጻሜ የክልሉ መንግስት ጠንካራ የክትትልና የድጋፍ ስርዓት በመዘርጋት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያደርጋል" ብለዋል።

የጎርጎራ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ፍስሃ አሰፋ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ የዲዛይን ስራ መጠናቀቁንና

ለመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታም አንድ ቢሊዮን ብር የተመደበ መሆኑን ተናግረዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ኃይለማርያም ጎርጎራና አካባቢው ለቱሪዝምና አግሮ ኢንዱስሪ

 ዘርፍ ዕምቅ የተፈጥሮ ሃብት ያለው ታሪካዊ ስፍራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ ቀጠናውን በማስተሳሰር ለሀገር በቀል ፕሮጀክቶች መስፋፋትና መጠናከር ፋና ወጊ የልማት መርሃ ግብር እንደሆነም አስረድተዋል።

በፕሮጀክቱ የማስጀመሪያ ስነስርዓት ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንን ጨምሮ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን ባለስለጣናትና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም