ትውልዱ የንባብ ባህልን በማሳደግ ኢትዮጵያን በሳይንስና ቴክኖሎጂ የመጠቀች ለማድረግ ሊተጋ ይገባል- ዶክተር ሙሉቀን አዳነ

73

ባህርዳር የካቲት 28/2013 (ኢዜአ) ትውልዱ የንባብ ባህልን በማሳደግ ኢትዮጵያን በሳይንስና ቴክኖሎጂ የመጠቀች ለማድረግ ሊተጋ ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ አስገነዘቡ።

በደብረ ታቦር ከተማ የንባብ ክበባት ምስረታና የንባብ ሳምንት ስነ ስርዓት ተካሂዷል።

ዶክተር ሙሉቀን በወቅቱ እንደገለጹት ትውልዱ ስለሃገሩ፣ ስለራሱና ማንነቱ ጠንቅቆ ለማወቅ እንዲሁም ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ከፍታዋ ለማሻገር  የንባብ ባህሉን  ሊያሳድግ  ይገባል።

ኢትዮጵያን በአሁኑ ዘመን ዓለም ከደረሰበት የሳይንስና ቴክኖሎጂ የምጥቀት ደረጃ በማሰለፍ በዘርፉ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንድትሆን ለማድረግ የአሁኑና የመጪው ትውልድን የንባብ ባህል ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የንባብ ባህሉ ያልዳበረ ማህበረሰብ የመጣበትን ታሪክ በአግባቡ ጠንቅቆ የማያውቅ ከመሆኑም በላይ አሁን እንዳጋጠመን ከመተባበር ይልቅ እርስ በእርስ የመጠላለፍ ክስተት እየሰፋ እንደሚሄድ አመላክተዋል።

"አባቶቻችን አንድነቷን አስጠብቀው ያቆዩትን ሀገር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ወደ ከፍታ  ማሻገር የምንችለው የንባብ ባህላችንን ማሳደግና ታሪክን በአግባቡ መረዳት ስንችል ነው " ብለዋል።

"ሰው ሲማር፣ ሲያውቅና የንባብ ባህሉን ማሳደግ ሲችል አስተሳሰቡ ያድጋል፣ ይለወጣል፣ ታጋሽና አስተዋይ በመሆኑ ሀገሩን፣ ማህበረሰቡንና አካባበቢውን ለመለወጥ የሚያስችል አቅም መፍጠር ይችላል" ሲሉም ተናግረዋል።

በተለይ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች በፌስቡክ በሚለቀቁ ያልተረጋገጡ ወሬዎች ከመጠመድ  ይልቅ መጻህፍትን በማንበብ ምክንያታዊነትን ለማዳበር መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ መጻህፍት ኤጀንሲ  ከደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋር  በመተባበር የንባብ ባህልን ለማሳደግ እያደረገ ያለው ጥረት የሚመሰገን መሆኑን ጠቅሰዋል።

የብሄራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻህፍት ኤጀንሲ ተወካይ  ዳይሬክተር አቶ አሳልፈው  ዓለም በበኩላቸው ኤጀንሲው በሀገራችን የንባብ ባህልን ለማሳደግ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በትግራይና በሌሎች ክልሎች የንባብ ባህልን ለማሳደግ በ1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የንባብ ክበባትን ማቋቋም ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ኤጀንሲው ከደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር  በደብረታቦር ከተማና  በፋርጣ  ወረዳ  በሚገኙ ሰባት 1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች  የንባብ ክበባት  ምስረታና  የንባብ ሳምንት እንዲጀመር ማድረጉን ጠቅሰዋል።

እንደ  ተወካይ ዳይሬክተሩ ገለጣ ኤጀንሲው ግምታቸው ከ157 ሺህ ብር  በላይ  የሆነ  ከ6  ሺህ  በላይ የተለያዩ መጻህፍቶችን ለአራት የህዝብ ቤተ-መፃህፍትና የንባብ ክበባት  ለተመሰረተባቸው ትምህርት ቤቶች በድጋፍ አስረክቧል።

"ንባብ ለሰው ልጆች አእምሮና ሰብዓዊነት መገንቢያ መሳሪያ ነው" ያሉት ደግሞ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ወንዴ መሰረት ናቸው።

በንባብ ክበባት ምስረታውና በንባብ ሳምንት ማስጀመሪያ ስነ- ስርአት ላይ የተገኙ ታዋቂ ደራሲያን ልምድና ተሞክሯቸውን ለተማሪዎቹ አካፍለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም