ለኢትዮጵያ አንድነትና እርቅ በእጅጉ እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለፁ

67

የካቲት 28/2013 (ኢዜአ) ለኢትዮጵያ አንድነትና እርቅ በእጅጉ እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተፃፈው 'የመደመር መንገድ' መፅሃፍ በአንድነት ፓርክ ትላንት ምሽት ለምረቃ በቅቷል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የመጽሐፉ ደራሲ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፣ ሚኒስትሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለኢትዮጵያ አንድነትና እርቅ በእጅጉ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እንድትበታተን እና እንድትፈርስ የሚፈልጉ ኃይሎች መኖራቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን እንደ ትላንቱ ከፋፍሎ መግዛት ነው የሚሻለው የሚል ሃሳብ እንደቀረበላቸው አጋርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውሮፓ ለሥራ በሄዱበት ወቅት ያገኙት ሰው "ኢትዮጵያን ለመግዛት የሚመቸው ስትከፋፍላት ነው" የሚል ሃሳብ እንዳቀረበላቸው ገልፀው እርሳቸው ይሄ ሀሳብ ለገዢዎች እንጂ ለአገልጋዮች እንደማይሆን እንደገለፁለት አስረድተዋል።

ብዙዎች የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት እንደማይፈልጉ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ማነው ይቅርታ የሚጠይቀው የሚለው ጉዳይ ብዙም አጨቃጫቂ አለመሆኑን እና ችግሩን በይቅርታ አልፎ ውጤቱ ላይ መድረስ ይገባል ነው ያሉት።

ይቅርታ የመጠይቅ ልብ ካለን የሚያጀግን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማነው ያጠፋው ማነው የሚጠየቀው የሚለውን ብቻ ማየት ሳይሆን በይቅርታ የምናተርፈውን ማሰብ ጠቃሚ ነው ብለዋል።

የብዙ ያደጉ አገራት የጀርባ አጥንት ይቅርታና አንድነት መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር አብይ ለዚህም የካናዳን፣የሩዋንዳ እና የደቡብ አፍሪካን ተሞክሮ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ተበዳይ ነኝ ብሎ የሚያስብ እንጂ ለአፍታ እንኳን በድዬ ይሆን እንዴ ብሎ የማይጠይቅ በመሆኑ ይቅርታን ውድ እንዳደረገው ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰላም ተጋዮችን በሚገባው ልክ ማወደስ ባለመቻሉ በግጭትና በሽብር የሚያምኑ ሰዎች እንዲጎሉ ማድረግ ችሏልና ይህ ነገር እንዲቀየር ብዙ መስራት ይገባል ነው ያሉት።

ይቅርታ ስንጠይቅ ወጣቶች ይሄንን በመማር በሰላምና በተስፋ ከሚያጋጩና ከሚያነታርኩ ጉዳዮች ወጥተው አገር ይገነባሉ ብለዋል።

ብዙውን ጊዜ ችግሮች አሊያም ምጡ እና ጭንቀቱ ላይ ብቻ ሳይሆን ውጤቱ ላይ አተኩረን መሄድ ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም